ወ/ሮዋ 30 ሚሊዮን ብር ረዱ! (ሶሎሞን ታምሩ)

ወ/ሮዋ 30 ሚሊዮን ብር ረዱ! (ሶሎሞን ታምሩ)

ሥልጣን በጠመንጃ በለስ ቀንቷቸው ከቤተ መንግሥት ገቡ። ሥልጣን የሕዝብ አደራ ሳይሆን የሌብነት ዋነኛ ምንጭ መሆኑን አስረገጡበት። ልብ በል! በዚች በ30 ሚሊዮን ብር የሕዝብ ሃብት ልገሳ ውስጥ ምን ያህል ቢሊዮን ብር እንዳለ አስተውል። እውን ወ/ሮዋ በመፅሃፉ የአሥራት አሰጣጥ ደንብ ብትሄድ እንኳን ከመቶ አስር ሰጡ ብለህ በትንሹ ብትነሳ እጃቸው ላይ ያለውን ጥሬ ገንዘብ በቅድመ አልጄብራ ትምህርት ቀመር አስበው።

የብር 4 ሺ የወር ደመወዝ እንዲህ ያበረከተላቸውን ጌታቸውን ዲያቢሎስን ለመከደም ዕጣን ማጨስ ትተው ለእግር ኳስ ፍቅራቸው እንዲህ ይለግሳሉ። አቤት ! እኒህ ሴት የመጀመሪያዋ የእግር ኳስ አፍቃሪ። ታሪክ ሰሩም ፃፉ። ባለቤታቸው እንኳን ደንታ አልነበራቸውም። እኚህ ከየት ተቀዱ? አሃ! ለካስ ትዳራቸው ፈርሷል። 80 ተቀዷል።

እዚያው አገር በ500 / 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በረሃብ ይቆላል። ሕፃናት ገርጥተውና ቀጭጨውም ይታያሉ። ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ዘጠነኛ/ አስረኛ ያደረገን ከብት ሃብት ልማት በድርቁ ምክንያት ከብቶች በፍጥነት በግጦሽ እጦትም እያለቁ ነው። ይሄን ዓይነት ደግነት አራዳው አባ ዱላ ይሆን ያስተማራቸው? ኦቦ አባ ዱላ ካለው ሕንፃ አንዱን ለኦ ፒ ዴ ኦ ሰጥቶ እንዳለፈ ታሪክ ተፅፏል። ድርጅቱ አባቱን በጣም ይወዳል። አፈር ይብላኝ እንዲህ ዓይነት ፍቅር። ምርኮኛ ሰርቶ አልፎለትና ምኞቱ ሰምሮለት እንዲህ ሲለግስ ደስ ይላል። ያለንን ሰጥተናልና ሙስና ምናምን አትበሉን ግብርም ቀረጥም አትጠይቁን ዓይነት።

ሴትዮዋን ግን እንዲህ ቁጠባ ነዋ ያዘመናቸው። ኢንዱስትሪያሊስት …የቢዝነስ ሴት…. ባለ ሃብት / ኢንቬስተር…. የነፃነት ተሟጋች…. የድኾች እናት…. አዛኚቱ ወለላይቱ… አንዳንዴ ይህ ባል የሚባለው የሴትን ልጅ ዕድገት ያቀጭጫል ልበል? እኒህ ሴት ሃዘን እያለባቸው እንኳን አልተበገሩም። ሌት ተቀን ደፋ ቀና ብለው ቱጃር ሆኑ። በለጸጉ። ተምሳሌት ሴት ሆኑ። እቤት ማማራቸው። እንግዲህ ባለ ጠጋ የሆነች ሴት የምትወድ ሁላ ጠጋ ጠጋ ብለህ እንጀራ ሳይሆን አነባበሮ ስራ።

ታዲያ መጽሐፍ ጥፈው ወይ አስጽፈው ተመክሮቸውን የማያስተምሩን? እትይዬ እባክዎትን ለርስዎ የዘነበው ለኛም ቲሆን ቲሆን ያካፋልን ታልሆነም ዳመና እየሰራ እንኳን በላያችን ላይ ያጉረምርምብን። ምን አልባትም እኮ ኢትዮጵያ በምትባል ምድር ቀድመን ተወልደን አፈር ፈጭተን አድገን ክርሶም ቀድመን ተምረን ለአገራችንም በረከታችንን ከርስዎ በፊትም ሰጥተን ይሆናል። ኑሯችን ግን ከሕዝባችን ኑሮ ፈቅ ያላላም አለን። ብዙ ነን። የሌብነት መንገድን የምንጠየፍና የምናወግዝ። የሌብነት ሃብት የማያጓጓን ሁሌም ያልተንገበገብንም ያልዘረፍንም። ኢትዮጵያ አገራችን ንፁህ እጆችና ኀሊና ያላቸው ያፈራቻቸው ልጆቿ ነፍ ናቸው ። ሞልቷታል።

ሥልጣን የአፍሪካ የቀማኛ ባለጸጎች ምንጭ ነች። የሚያስቀው ግን እነርሱ ባለ ጠጋ ሲሆኑ የበለጸገች ኢትዮጵያ እያልን ሕዝብ የምናደነቁር ምሁር ተብዬዎችና ትንንሽ ቦርጭ የጀመረን ሙሉ ልብስ የለበስንና የተጫማን ምንአልባትም መኪና የነዳን የገንዘብ ችግር የሌለብንና በጥቅም የተሳሰርን የበቀልንበትን ሕዝብ በፍጥነት ክደን ስራ ማለት ትርጉሙ ሳይገባን እያጭበረበርን ለመኖር የምንከጅል ካድሬ ቢጤ ባለ ዲግሪዎች ነን።

የበለፀገች አዜብና መሰሎቿ እንጂ የበለፀገች ኢትዮጵያ የለችም። ሳታጣ ያጣች የደኸየች ኢትዮጵያ ግን ከነልጆቿ አለች።

(ሶሎሞን ታምሩ)

Leave a Comment