ጉዞዬ ክፍል ስምንት | በያሬድ ይልማ

ጉዞዬ ክፍል ስምንት

Konso Wakkas

የኮንሶን መስህቦች ተዘዋውረን አይተን ወዳ አመሻሹ ላይ እድገት ሆቴል ተመልሰን ለእንግዶቻችን እራት ቆንጆ መላ ዘየድን፡፡ ከሆቴሉ ገራገር የኪችን ሰራተኞች ጋር ተነጋግረን፣ እንግዶች እራታቸውን የሸክላ ጥብስ እንዲበሉ አድርገን የቀኑን ስራ አጠናቀቅን፡፡ ማታ ላይ ከኩባ ተማሪው ሳሚ ጋር አብረን ተቀምጠን ቢራ እየጠጣን ፣ በሶማሊያና በኢትዮጵያ ጦርነት ማግስት እንዴት ከሃረር ወደ ኩባ እንደሄደ እያወጋኝ የተዋወቅንበት፣ እንዲሁ ታዲያ እኔም በልጅነቴ ማንም ሳይፈርድብኝ እንዳሻኝ ቢራ እየጠጣሁ ማምሸት እንደምችል ነፃነቴን ያረጋገጥኩት ነበር፡፡ ምንም እንኳን የሚያኩራራ ነፃነት ባይሆንም፤

እንዲህ እንዲያ እያልን ፣ ሳሚ ጨዋታ ጨዋታውን እያሰበ እያወራኝ እኔ ቢራ ቢራዬን እያሰብኩ እየጨለጥኩ በሆቴሉ ተቀምጠን ፣ ሁለት የከተማዋ ልጆች ሳሚን ሰላም ብለዉት፣ ከፈረንጆች ጋር ስለምትሰሩ እስኪ የሚገዙ ከሆነ ጠይቁልን፣ የከበረ ማእድን አለን-“ሳፋየር” ሚባል ብለው ሰማያዊ የሚያብረቀርቅ ነገር ቋጠሮ ፈትተው አሳዩን ሳሚ ወዲያው በስጨት ነገር ብሎ፣ “ማነህ ጋሼ እና ይዘን የመጣነው አገር ጎብኚ እንጂ የሜርኩሪ ደላሎችን አይደለም! እንደዚህ አይነት ነገር አይፈልጉም!” ብሎ መለሰላቸው፤ ታዲያ ሌላኛው ልጅ እጂን ወደ ብልቱ አካባቢ አስገብቶ አወጣ፤ በጎርጊስ ሞቅታ መነቃቃት ጀምሮ የነበረው አይኔ በድንጋጤ ተበለጠጠ፡፡

ልጁ ከውስጥ ሱሪው ውስጥ ሽጉጥ አውጥቶ ወደሳሚ እያየ፣ “እሺ እናንተስ ሽጉጥ አትገዙኝም ርካሽ ነው” አለ፡፡ ሳሚ ወደኔ ዞሮ “አንተ ትፈልጋለህ” አለኝ፣ “እንዴ! እኔ ምን ሊያረግልኝ ሳሚዬ!” ንግግሬን ሳልጨርስ ሳሚ ወደ ልጆቹ ዞሮ “ሌላ ጊዜ” ብሎ ልጆቹን ሸኛቸው፡፡ ይሄንን ቢራ ታዲያ ከሆቴሉ ባለቤት ጋርም ጭምር እየተገባበዝን ስንለጋ አምሽተን አደርን፡፡ ቅር ቅር ሲለኝ የነበረው አንድ ነገር የገብሬ ነገር ነው፤ ከጉብኝቱ ከተመለስን በኋላ አላየሁትም፣ እንደዛው ሳንተያይ ተኛን፡፡

እሁድ ማታ ለሰኞ አጥቢያ ከእድገት የኪችን ሰዎች ጋር ባደረግነው የቅድሚያ ትእዛዝ መሰረት ጠዋት ለእንግዶቻችን የእንቁላል ፍርፍር እና ትኩስ ነገር ከሆቴሉ፣ ሌሎች የሚበሉ ነገሮችን ፣ እንደ ማርማላት የዳቦ ቅቤ፣ የሚቀባ ቾኮላት እና ማር ካዲስ አበባ ይዘን ስለመጣን፣ በጠረቤዛ ላይ አድርገን አቅርበን ደስ ብሎን ተመገብን፡፡ ለራሴም ቢሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈረንጅ ቁርስ ምን ሊመስል እንደሚችል ግልፅ ምስል ያገኘሁት በዚሁ እለት ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ የእንግዶችን ቁርስ ትእዛዝ በምከታተልበት ሰአት በኪችኑ ያለችው ካቦ፣ አስተነጋጅ ታዞ ለረጅም ሰአት ያልተወሰደ በያይነቱ እንዳየ፣ “ኢሄ ባያይኔት ኢስካሁን ኢዚ ኖ!? ሲል “ኢና ታዳ ኣንቴ ማጥቴ ካሎሰድኪ ባያይኔት ኢጊር ኣሎ ኢንዴ ኢራሱ ሚሄድ!” ብላ የመለሰችው ይቺው ካቦ ሌላ የማልረሳውን ንግግር ገብሬን በተመለከተ ተናገረች፡፡

የሆቴሉን ክፍሎች ከምታፀዳው ሳቂታ ሴትዮ ጋር እያወራች ልክ እኔን ስታየኝ የፌዝ ሳቅ ከሴትየዋ ጋር እየተሳሳቀች፣ “ኢናንቴ ጋር የማጡት ሳውዬ፣ ማልካቸው ቢቻ ናው ሃይሌስላሴን ሚማስሉ እኒጂ ጉልበታቼው የሃይሌ ጋብራሲላሴ ናው!” ብላ አሹፋ ኢሄሄሄሂሂ… ብላ ሳቀች፡፡ ምንም ስላልገባኝ የሚበላውን ይዤ ሄድኩኝ፤ ሳሚ ጋር ደርሼ ልበላ ስቀመጥ ከትላንት ጀምሮ ያላየሁት ገብሬ ጥድፍ ጥድፍ እያለ መጥቶ “ሳሚዬ ያቺ የሰጠኸኝ የዶርዜ አረቄኮ ማታ ተደፋችብኝ! እንደው ትንሽ ካለህ ትጨምርልኛለህ!” አለው፡፡ እንግዲህ ባይምሮዬ ያሰብኩትን እናንተም የምታስቡ ይመስለኛል፡፡

በዚህ ቀን ጉዞ ከመቶ ሰማንያ በላይ ኪሎሜትሮችን ያክል መንገድ እናካልላለን፡፡ የኦሞ ሸለቆ የሚባለውና ሞቃታማውን የአገራችንን፣ እንዲሁም የዚህ ጉዞ ዋነኛ ትኩረት የሆነውን አካባቢም ማየት የምንጀምረው ከዚህ በኋላ ነበርና፣ እኔ ጓጉቿለሁ፡፡ ገብሬ ትንሽ ሰግቷል፤ የቱኤች ሾፌራችን ግን ብርክ ብርክ ይዞታል ማለት ይቻላል፡፡ከኮንሶ በጠዋት ወጥተን ለሰላሳ ያክል ኪሎሜትሮች ከኮንሶ ከተማ ወጥተን ለሁለተኛ ጊዜ ደልቤና በሚባል ወንዝ ውስጥ መኪናችንን ዋኝቶ አለፈ፡፡ የስምጥ ሸለቆን የረባዳነት ጉዞ ገትቶ ተራራማ የሚያደርገውን የኮንሶን አካባቢ በሚጥመለመል የተራራ ላይ መንገድ ሄደን የኦሞ ሸለቆ አካል የሆነው የወይጦ በረኀ ጋር ቆመን የሚቀጥሉትን ጥቂት ቀናቶች የምናሳልፍባቸውን አካባቢዎች በርቀትም ቢሆን ካምባ ላይ ሆነን አየን፡፡

River crossing at Omo

ከዚህ ስፍራ እስከ ወይጦ ወንዝ ድረስ የሄድነው መንገድ አስቸጋሪ የሚባል መንገድ እና ሰው የሚባል ነገር የሌለበት ነበር፡፡ ወይጦ ወንዝን መኪና እንዲሻገርበት፣ ከጥቂት ብረት እና ከብዙ እንጨት የተሰራው ድልድይን ፣ ተፈትሾ እንጂ ዝም ብሎ ማለፍ አይቻልም፡፡ ካዲስአበባ ስንነሳ ይዘን የመጣነውን የድርጅታችን ደብዳቤ ላይ የተፃፈውን የመኪኖቹን ታርጋ፣ የሾፌሮች ስም፣ እና የእንግዶችን ቁጥር የያዘ ደብዳቤ የወይጦ ድልድይ ላይ ከነበሩት ጠባቂዎች ላንዱ ሰጥተን ቆምን፡፡ መቼም ጠባቂው የመኪኖቹን ታርጋ አጣራ ሳይሆን የሚባለው፣ ቁጥሮቹን አንድ ባንድ ቆጠራቸው ነው የሚባለው፡፡

Beauty of Omo Tribes

ከፍተሻው አልፈን የሚሰበር የሚመስለውን ድልድይ የነሳሚን መኪና ተከትለን ሄድን፡፡ ቱኤቹ መኪናችንን ድልድዩን አልፎ ባለው ፈታኝ ዳገት ልክ እንደ ጨንቻው ትንሽ ከመፈተኑ ውጪ ሌላ ችግር ሳይደርሰብን የበረሃዋ ገነት ወይጦ መንደር ደረስን፡፡ ከኮንሶ በመጠኑም ቢሆን ነፋሻ የአየር ሁኔታ ካለው ስፍራ ተነስተን ወደ ኦሞ ሸለቆ በመውረዳችን አስገራሚ በሚባል ልዩነት ሊቀመጥ የሚችል፣ ሞቃት አየር እየለበለበን ወይጦ ስነደርስ፣ ይቺ አንድ ምግብ ቤት ያለባት ስፍራ በጀነሬተር የሚሰራ ፍሪጅ ያለበት ስፍራ ስለነበር፣ ለእንግዶቻችን ፣ ሳሚና ገብሬ ቀዝቃዛ ቢራ፣ ለእኔና የቱኤች ሾፌራችን ቀዝቃዛ ሚሪንዳ ጭልጥ አድርገን እፎይ በሚያሰኘው ቀዝቃዛ ጎጆ ማረፊያ ጥቂትም ብትሆን እረፍት አደረግን፡፡ የኦሞ ሸለቆ ብሄሮችንም እዚሁ ወይጦ ላይ ነው ያየነው፡፡ “ፀማይ” ተብለው የሚጠሩትን ለእናቴ መጠሪያ ፀሃይ ቅርበት ያላቸውን ውብ ህዝቦች የፊት የፀጉር እንዲሁም አለባበስ ይኼው እስከዛሬ ከህሊናዬ ተጣብቆ ተቀምጧል፡፡

መልካቸው ወደ ጠይምነት የሚሄደው ያየኋቸው ሴቶች፣ ፀጉራቸው በሚያስገርም መልኩ ሉጫ ነበር፡፡ በእዚህ ሃቅ ተደንቀ የደረቡትን የቆዳ ልበባስ እና አጠቃላይ መልካቸውን እያሰብኩ መንገዱን እየተምዘገዘግን ሄደን አንድ መንደር መሳይ ስፍራ ላይ ደረስን፡፡ ይህ ስፍራ ላይ ወዲያው ማንም የሚያስተውለው ነገረ ቀይ የሆነውን መግቢያያ አካባቢ ያለውን አፈር ነው! አፈሩን አይቼ ቀና ስል፣ ቀይአፈር የሚል በላሜራ ላይ የተፃፈውን የከተማዋን ስያሜ አየሁ፡፡ ትንሷን የበናዎችን ቀይአፈርን አልፈናት መንገዳችንን ቀጠለልን፡፡ ጥቂት እንደሄድን ግን በየእለቱ የሚከተለን የህፃናት የተለያዩ ስጦታዎችን ፍለጋ የሚያደርጉት ትርኢት መልኩን ከዳንስ ወደ ሰርከስ ትእይንት ቀይሮ በቀይአፈር ጠበቀን፤ ህፃናቱ በጠቅላላ ሰውነታቸውን በተለያዩ የአፈር ቀለማት አስውበው፣ ረጃጅም እንጨቶች ላይ ሆነው እየተራመዱ አሳዩን፣ አስገራሚ ነበር፡፡ ከሃይላንድ እስከ ከረሜላና ምላጭ የደረሳቸው ስጦታዎች ናቸው፡፡ እነኚህ ስጦታዎች በሳሚ የግዢ ምክር የተደረጉ ናቸው፡፡

Boys in Benna

ቀይአፈርን አልፈን አርባ ያክል ኪሎሜትር ልናገባድድ ስንል ያልጠበቅኩት ነፋሻ አየር መንገዳችንን ተረከበና ጂንካ ገባን፡፡ በዚህ ሞቃት የኦሞ ሸለቆ ጉዞ የጂንካን ነፋሻነት እንዲሁም የአረንጓዴ ተክሎች ሽፋን ጠንቋይ ካልሆነ በስተቀር መገመት ኤቻልም፡፡ ምሳ ሳንበላ ሰአቱ ስምንት ሰአት ተቃርቦ ስለነበር ለእንግዶች ጥሩ ምግብ ይገኝበታል በተባለው ኦሪት ሆቴል ያገኘነውን ልናበላ ወስደን፣ ለሁሉም በያይነት አዘንላቸው እኛ ደግሞ ለብቻችን ልንበላ ወደ ኦሪት ሆቴል በረንዳ ወጣን፡፡ እኛ ጥብስ ካልበላን የበላን ስለማይመስለን ሸሸን፡፡

አራታችንም ባንድ ላይ ተቀምጠን የየራሳችንን ስናዝ፣ ሳሚ ክትፎ አዘዘ፤ ሁላችንም ክትፎውን እንዴት እዚህ አዞ ይበላል፤ ትንሽ አይፈራም፣ ቅቤውንስ፣ ስጋውንስ ቢሆን በውስጣችን እየተገረምን ስንመለከተው፣ ሁኔታችንን ያነበበው ሳሚ፣ የጂንካ ክትፎ ኢትጵያ ውስጥ ከጉራጌ ቀጥሎ ተወዳዳሪ የሌለው ነው አለና ምክንያቱን ነገረን፡፡ አስተናጋጁ የሚጠጣ ታዞን ምግቦቹን ይዞ ሊመጣ ጥቂት እንደታመደ ሳሚ የሆነ ነገር ትዝ ብሎት፣ “ማነህ ወንድሜ!” ብሎ አስተናጋጁን ተጣርቶ አስቆመው፣ በረንዳው አካባቢ ያለ ሰው በጠቅላላ ሰምቷል የሳሚን ድምፅ፣ “ማነህ ወንድሜ ክትፎው ላይ የምታደርገው ቅቤ ጠብ ነው ላመል እንጀ ለሌላው እንደምታደርገው አልፈልግም!” አለና ዞር ብሎ፣ አለበለዚያ ግማሽ ሰሃን ቅቤ ግማሽ ሰሃን ክትፎ ሆኖ ተጥለቅልቆ ነው የሚመጣልኝ አለን ለኛ፤ ወዲያው ሌላ ሰው ደግሞ አስተናጋጁን ተጣራና አስቆመው፣ ከኛ አለፍ ብሎ ያለ ወንበር ላይ የነበሩ እንደኛው ምግብ ተስተናጋጆች ነበሩ፤ “ኣሰላፊ፣ ኣሰላፊ፣ የሰውዬ የክትፎ ቅቤ እኔ ሳሃን ላይ ጨምሬህ አምጣልኝ! ሂሳብ ኣዴል እንዴ” ብሎ ሳሚን ዞሮ ፈገግ እያለ እያየ ጠቀሰው፡፡

ይቀጥላል!

በያሬድ ይልማ

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!

Leave a Comment