ጉዞዬ ክፍል አስራ ሁለት | በያሬድ ይልማ

በአማርኛ ቋንቋ ብቃት በጣም ከሚገረሙቱ መካከል ስለሆንኩ፣ ቋንቋው ላይ ችግር እንደሌለ እረዳለሁ፣ አንዳንዴ አማርኛም በጥቅማቸው ልክ ተመጣጥነው ያልተሰጡ ቃላት ቢኖሩም ማለቴ ነው፤ ለምሳሌ ያክል አማርኛ ህይወታችን ለሆነው “ዳቦ” ሁለት ፊደል መድቦ “ለቁርጭምጭሚት” ሰባት ቃል ያባክናል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ጥንካሬው እንጂ ድክመቱ አይጎላብኝም፡፡ ግን አንዳንዴ ፣ በተለይ የቦታ መጠሪያዎችን ሳይ አማርኛውን ባግባቡና በአቅሙ ልክ መጠቀም ያልቻሉ፣ ወይ ደግሞ የሌላ ቋንቋ ቃል ስያሜውን ቀጥታ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በማምጣት ሰንካላ ስያሜ ተሰጥተው ማስተዋል ይቻላል፡፡ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ፣ የእንግሊዘኛውን ቃል፣ “ኦሞ ቫሊ- Omo Valley” በቀጥታ ወዳማርኛ “የኦሞ ሸለቆ” ብሎ የተረጎመው፣ ሰው በኢትዮጵያ የውበት ኤደን ላይ ከፍተኛ በደል በመፈፀሙ፣  በራሱ በኦሞ ወንዝ ውሃ የተበጠበጠ ኦሞ ሲጋት ማየት የግል ምኞቴ ነው፡፡ በምክንያት ይሁን ንግግርህ ካላችሁኝም፣ የኦሞን አካባቢ አቀማመጥ እንጂ ፣ የተቀመጠበትን እንቁ ህዝብና ተፈጥሮ፤ በኚህ እንቁ ህዝቦች መካከል ያለውን አስገራሚ ልዩነት እና አንድነት እንደኔ ገርመም ላደረገ እንኳ ይህ ስም “እንቁዋ” የሚል ኦሞን የሚገልፅ ቅጥያ ከስያሜው ፊት እንደሚቀረው ይረዳል፡፡

ኦሞ በሄድኩኝ በስድስተኛ ቀኔ ለዚህ “የኦሞ ሸለቆ” ለሚል ስያሜ ዋነኛ መነሻ የሆነውን ወንዝ “ኦሞን” ለመጀመሪያ ጊዜ አየው ዘንድ የወሰደኝ ፈታኝና አዙሪታም መንገድ ዛሬ አስራ አራት አመታት አልፈው፣ ከምድሪቱ በታች ፈሳሽ እንቁ አለበት ተብሎ መዘጋቱ ደግሞ የኦሞን የእንቁ ምድርነት ብቻ ሳይሆን የጋይዳችን ሳሚን ነብይነት እንድገረም አድርጎ ያስረዳኛል፡፡ በዚሁ ቀን ጉዟችን የምናድረው ፣ “ካሮ” የሚባሉት የኦሞ ነዋሪዎች ስፍራ በሆነው ሙሩሌ የሚባል አስገራሚ ማረፊያ ነበር፡፡ ይህ ስፍራም በቱሪዝም ህይወቴ ፈፅሞ ልረሳቸው የማልችላቸውን፣ ይልቁንስ እምሳሳላቸውን ትዝታዎችን የማሳልፍበት፣ ወዳጆች የማፈራበት የአመታት ቤቴ እንደሚሆን ቅንጣት ፍንጭ እንኳ አልነበረኝም፣ ግን እውነታዬ እንዲህ ነው፣ ሙሩሌ ቤቴ ይሆንና ባየር በመኪና ፣ ከዚህ በኋላ እመላለስበታለሁ፡፡

ሁለት ቀናትን ካሳለፍንበት የማጎ ፓርክ ቆይታችን በጠዋት ተነስተን፣ የገብሬን ኮብራ ሳሚ ጋይዳችን ከቱኤች ጋቢና ተቀምጦ ከፊት እየመራን፣ ጉዞ ወደ ካሮ ምድር ማልደን ጀመርን፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ ስለገሃነም የሚያስረዳበት ክፍሉ ላይ ፣ እነሆ ህዝቡን በእሳት እና በአቧራ እቀጣቸዋለሁ የሚል ገለፃ ይኑር አይኑር እርግጠኛ አይደለሁም፣ ግን ገሃነብ መባል ካለበት፣ አቧራ ሊኖረው ይገባል ባይ ነኝ! መጥኔ ላገሬ ወፍጮ ፈጪዎች እንጂ፣ እንዲህ እንደ “ለቡክ” መንገድ አይነት የአቧራ መንገድ ለጠላትም አይስጥ፡፡ የሚገርመው ደግሞ፣ እንደ ጭስ እየበነነ፣ በመኪናዋ አፍና ቂጥ ገብቶ “የእኛንም” ማፈኑ ሳያንስ፣ መኪናችንን (በተለይ ቱኤቿን) እንደ ዶሮ ፈንግል በየአንድ ኪሎ ሜትሩ አቧራው እንደ ጭቃ አንቆ ሲያዳፋት ብታዩልኝ፣ የእዚህ ቀን ስቃያችንን ትረዱኝ ነበር፡፡

ታዲያ እንዲህ እንደጭቃ በሚያንቅ የአቧራ መንገድ በምትያዘው መኪናችን ምክንያት ከፍተኛውን ስቃይ የቀመስነው፣ ያ ምስኪን የቱኤች ሾፌርና እኔው ነን፡፡ ሾፌሩ ያው በተደጋጋሚ የምትያዝ የነበረችው የሱ መኪና ስለሆነች፣ ጭንቁም ንዴትና የጉልበት ብክነቱም የእሱ ከፍ ማለቱ አይቀሬ ነው! ከሱ ለጥቄ ግን ገፈት ቀማሽ እኔ ነበርኩ፡፡ የልጅ ነገር በመጀመሪያው መኪናው አቧራ ውስጥ ሲቀረቀር፣ ከኋላ ከነበረው መኪናችን ላይ ዘልዬ ወርጄ አካፋ እንኳን ሲሰጠኝ እንቢ ብዬ፣ ይሄንን ፊኖ አቧራ በእጄ ከመኪናው ስር እዝቅ ጀመረ፡፡ “ይቺ ዘለል፣ ዘለል” አለ ያገሬ ሰው ብዙ ስለሚያውቅ፤ ያ ቱኤች ታዲያ መጀመሪያ ከተያዘበት ስፍራ በኋላ በቃ ዝም ብሎ እየሄደ አቧራ ውስጥ መቀርቀርን ስራው ሲያደርግ ፣ ሳሚ አላጋጭ፣ ገብሬ አዛዥና ተቆጪ ካቦ ፣ ቀልቃላው እኔ ደግሞ አቧራ ቆፋሪ ሆኜ ተሾምኩና የገሃነብ ቆይታን በኦሞ አጣጣምኩኝ፡፡

በዚህ የምሬት ቁፋሮ ወቅት ነው ታዲያ ሳሚ ትንቢት የተናገረው፤ ልክ የለቡክን ፈታኝ የሰአታት ስቃይና የአቧራ መንገድ አገባድደን፣ መኪኖቹ በአሸዋማ መንገድ ላይ መሄድ ሲጀምሩ ፣ ማመን ስላቃተኝ ሳሚን ጠየቅኩት ፤ ሳሚዬ እውነት ይሄ የአቧራ መንገድ ተጠናቅቋል!? ከዚ በኋላ ያንን የገሃነብ ስቃይ ደግሜ አላይም” ብዬ በሬድዮ ስጠይቀው፣ ገሃነብ አልከው ያሬድ!  ጀናባ ነው እንጂ ብሎ ጀመረ፡፡ ትላንት እዛ ቆምባ የሙርሲ መንደር በነበረውን የብልትና ጡት ኤግዚቢሽን ወስዋስ ማጎ የተመለሱት ፣ እኔጋር ያሉት ባልና ሚስቶች ያረጉትን አድርገው ውሃ ሳይነካቸው መኪና ላይ ወጥተው ነው፣ ኦሞ ምን ያድርግ ብለህ ነው፣ የእነዚ የባልና ሚስቶቹ ጀናባ ነው ስቃይ ያመጣብን እንጂ ኦሞማ አፈሩ ሁሉ ወርቅ፣ ዛሬ እያለፍክ እያለፍክ የቆፈርከውን ጉድጓድ ደግሞ አንድ ቦታ ላይ አድርገኸው ቢሆን ኖሮ ነዳጅ ታወጣ ነበር ብሎ አፌዘ! ከተወሰኑ አመታት በፊት ፣ ሌላ ቦታ ሳይሆን ይኸው ስፍራ እራሱ በነዳጅ ፈላጊዎች ተከልሎ ተዘጋ፤ የሳሚ ትንቢት!

Murrulle camp site

ከበራሪ ህፃናት፣ እልፍ አእላፍ ቶን አቧራ፣ ሰማይ ድረስ የሚዘሉ ወንዶች፣ ከከንፈራቸው ስር በሚስማር ተበስተው ሚስማር በቀዳዳው ውስጥ ጨምረው በሚያጌጡ የቆርጮና የለቡክ ነዋሪዎች እንዲሁም ታላቁና ባለ ቢጫ ቀለም ውሃ ተሸክሞ ኪንያ የሚያደርሰው ወንዛችን ኦሞ ተደማማራ የተሰራችውን የካሮዎች መኖሪያ በሁለቱ መኪኖቻችን ከሰአት በኋላ ሙሩሌ ካምፕ ደረስን፡፡

የካሮዎች መኖሪያ አካባቢ መድረሳችንን ያወቅነው ያው እንደተለመደው፣ የፈረንጅ መኪናን ሲያዩ በሚያብዱት የዚህ አካባቢ ህፃናት ነው፡፡ የካሮ ህፃናቶች በሌሎቹ መንደሮች ካየናቸው የሚለዩት በፍላጎታቸው ነው፡፡ ሌሎቹ አላማቸው ወይ ደንሰው፣ ወይ የሆነ ነገር ጠይቀው ለመቀበል ነበር፣ መኪናችንን የሚከተሉት፤ የካሮዎቹ ህፃናት ግን መኪኖቻችንን የምር ለመቅደም ነበር የሚሮጡት፡፡ ካሮዎች ከኦሞ ብሄሮች በይበልጥ የሚታወቁት፣ ሰውነታቸውን በነጭ፣ ሃምራዊና ቀይ ቀለም ባላቸው ከተፈጥሮአዊ አፈር በሚሰሩ ውህዶች፣ መላ ሰውነታቸውን፣ በሚገርም የእርስ በእርስ አቀባብ ችሎታቸው፣ የጅግራን መልክ በሚመስል አኳኀን የሰውነት አጋጌጣቸው ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ይሄንን አቀባብ ለምን እና እንዴት ጀመሩ የሚለውን ግን፣ ከሳሚ ተረት ልረዳ ችያለሁ፡፡ በካሮዎች ዘንድ ፍቅርና ጀግንነትን የሚወክሉ ሁለት እንሰሶች አሉ፡፡ ካሮዎችም ከሰውነት አጋጌጣቸው እስከ አጨፋፈራቸው ድረስ በመልክም ሆነ በእቅስቃሴ መምሰል የሚሞክሩት እነዚሁኑ ፣ ፍቅርና ጀግንነትን የሚወክሉ እንሰሶችን ነው፡፡ እኒህም ሰጎንና ጅግራ ናቸው፡፡ ካሮዎች በመልክ የፍቅር ተምሳሌቷ “ጅግራን” ሰውነታቸውን በመቀባት ሲቀዱ፣ “ሰጎንን” ደግሞ በዳንሳቸው ይመስሏታል፡፡

አመሻሽ ስለበርና መብላት ስለነበረብን ድንኳን ተረባርበን ከጣልን በኋላ አንድ ረዳ ፍለጋ ወደ ማረፊያ ምግብ መብያ አካባቢ የውሃ ጀሪካን ይዘን እኔና ሳሚ ሄድን፡፡ የኦሞን ወንዝ ላየ ሰው ይሄንን በአፈር ብዛት ውሃ መቼም እንኳን ለምግብ መስሪያ ለማጠቢያም አንጠቀመም፣ ግን ንጹህ ውሃ ከየት አምጥተን እያልኩ ሳስብ ለነበርኩት ለእኔ ሴፖ የሚባል አስማተኛ ጠበቀኝ፡፡ ሙሩሌ የሚባለው ማረፊያ ስፍራ ተቀጣሪ ስለነበር፣ እኛ ስናገኘው ፍየል ሊያርድ እየተዘጋጀ ነበር፡፡ ሴፖ ፍየሏን ሲያርድ እኔና ሳሚ ፊት ለፊቱ ቆመን ጠበቅነው፡፡ የፍየሉን አንገት ባንዴ በስሉ ቢላዋ ከቆረጠ በኋላ መሬት ላይ ከሚንፈራፈረው የፍየል አንገት ደሙ ፊን እያለ ሲፈስ ሴፖ ቢላውን መሬት ላይ ጥሎ ወደ መሬት እሱም ተወርውሮ ፊን የሚለው የፍየሏ አንገት ላይ እንደቫምፓየር ተሰክቶ ደሟን መምጠጥ ጀመረ፡፡ አልዘገነነኝ ልበላችሁ! ታዲያ ሴፖ አፉ ላይ ፈርስ ሲመጣበት እቱፍ፣ እቱፍ እያለ ከፍየሏ አንገት ላይ እየተነሳ፣ “ይሄ ሌካሮ ዳንብ ናው” አለን፡፡

አማርኛ አቀላጥፎ ስለሚናገር ለስራችን ረዳት ልናደርገው ከተነጋገርን በኋላ ፣ ንፁህ ውሃ ከየት ነው የሚገኘው ቧንቧ ከሌለ ስለው፣ ችግር የሌም ተከተለኝ ብሎኝ፣ ጎራዳ በርሜል ውስጥ ወደ ተሞላው ቢጫው የኦሞ ውሃ ይዞኝ ሄዶ አንድ የዛፍ ስር ቢጤ እንጨት አመጣ፡፡ “ሲማ ይሄ “ኩልፎ” ታብሏል፡፡ የካሮ መዳኒት ኖው” አለኝና እንጨቱን በቢጫ ውሃ በተሞላው ጉርድ በርሜል ውስጥ ጨምሮ ለአስር ሰኮንድ ያክል ባንድ አቅጣጫ አማስሎ እንጨቱን ከውሃ ውስጥ አወጣው፡፡ በሰኮንዶች ውስጥ ድፍርሱ ያደረገው የኦሞ አፈር እያየሁት ወደ በርሜሉ ስር አስማት በሚመስል መልኩ ባንዴ ዘቅጦ ኩልል ያለ ውሃ ሆነ፡፡

አስማተኛው ሴፖ ታዲያ በዚህ ምሽት ረዳታችን ሆነና ከእኛ ጋር አመሸ፡፡ ምግብ ለሚዘጋጅበት ውሃ ቀድቶ ማምጣትም ሆነ እቃ ማጠብን በደንብ አድርጎ የሚችለው ሴፖ ፣ ከሁለት ድርጊቶቹ ውጪ፣ ካነጋገር እስከ ቁመናና ንቃቱ እንዲሁም ነገረ ስራው ሁሉ የሚገርም ካሮ ነበር፤ ብቻ የመጀመሪያው ያልተመቸኝ ነገር፣ አቀማመጡ ነው፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ሴፖ የለበሰው ብቸኛ ልብስ ጥቁር የሴት ውስጥ ልብስ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ለእንግዶች መቀመጫ ያመጣነው ወንበር ላይ ሲቀመጥ ታዲያ፣ የለበሰውን ውስጥ ልብስ ወደላይ ገልጦ ከፊት “ቁን” ከኋላ “ቂውን” ለተመልካች ክፍት አድርጎ ያመጣነው ወንበር ላይ ይቀመጣል፣ ሁለት ጊዜ እንደዚህ ሲያደርግ አይቼው፣ በሶስተኛ እንደሱ ለምን ታደርጋለህ ዝምብለህ አትቀመጥም ወይ ስለው፣ “ሊስብ (ልብስ) ኢንዳያልቅ ኢኮ ኖው” አለኝ፤ ይሁን ብዬ እሱን ካለፍኩት በኋላ ፣ ደጋግሞ ፊትለፊታችን ምራቁን “ኣኣክ” እያለ ይተፋል፤ አንተ ለምን ሰው ፊት እንደዚህ “ኣኣክ” እያልክ ትተፋለህ ሴፖ ነውር ነው እንደሱ” ስለው፣ በሚችላት የምትጣፍጥ አማርኛ “ኢህ፣ ናው ኢንዴ! ኢና ታዲ እንዳማራ ባሽታ ሊዋጥልህ እንዴ፣ ኢኔ ኢኮ ካሮ ናው ኢንጂ ኣማራ ናው!” ብሎ ደግሞ ፊት ለፊቴ በድጋሚ ሲለጥፈው፣ ምን ላርግ ተውኩት፡፡ ኋላ ሳስበው እውነትም መትፋት የነበረብንን ይሆን እንዴ ለግብረ ገብ ብለን እየዋጥን ያለነው ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡

ይቀጥላል!

 

በያሬድ ይልማ

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!

Leave a Comment