ጉዞዬ ክፍል አስራ ሶስት | በያሬድ ይልማ

Hammer Girl

በካሮዎች የምሽት ጭፈራ የተገባደደው የሙሩሌ አመሻሼ፣ የተደበደብኩ ያክል ቆስሎ ለነበረው እና ጭልጥ ባለ እንቅልፍ ለሚያርፈው ሰውነቴ ጥሩ የትእይንት መዝጊያው ነበር፡፡ ነግቶ ታዲያ በጠዋት እዚያው በሙሩሌ ካምፕ ሳይት ያየሁት እና አባቴ ተናዶ ሰው ሲሳደብ ብቻ በስም አውቀው የነበረ “አርጃኖ” የሚባል አስፈሪ እንሰሳ ከእንቅልፌ ከመነሳቴ በማረፊያው በማየቴ ንቅት ብዬ የቱርሚን መንገድ ጀመርኩ፡፡ከሙሩሌ በኋላ ለሶስት ቀናት የምናርፈው በሃመሮች አገር ቱርሚ ነበርና፣ ከሙሩሌ ተነስቶ እስከ ቱርሚ ድረስ ለሃምሳ ሶስት ያክል ኪሎሜትሮች የሚዘረጋውን አጭር ግን ደግሞ የማያልቅ ፣ ሌላ አስቸጋሪ መንገድ ማለፍ የግድ ነበር፡፡ በዚህ እለት ታዲያ በመኪናችን ውስጥ የነበረችው ስኮትላንዳዊ እንግዳ ለእኔ የኦርኒቶሎጂ የፊልድ ትምህርት ባድናቆት የምቀበልበት ቀን ነበር፡፡ በሙሩሌ ማረፊያ ከነበሩት የሚያብረቀርቅ ሰማያዊ ቀለም ከተላበሱትና፣ የእንግሊዝን የመገበያያ ገንዘብ፣ “ስተርሊንግን” መጠሪያቸው አድርገው በእንቁዋ የኦሞ ሸለቆ ከሚኖሩት ትናንሽ ወፎች፣ እስከ ሴክሬታሪና ባስታርድ የተባሉ የወፎቹን መጠሪያዎች በዚህች እገራሚ ስኮትላንዳዊት ሴት የወፎች እውቀት እየተገረምኩ አዲስ ዝንባሌ እየተማርኩኝ መንገዴን ጀመርኩ፡፡

ከሴክሬታሪበርድ (“ፀሀፊዋ”) እስከ ኮሪባስታርድ (“የኮሪ ዲቃላ”) ከስተርሊንግ እስከ ቢኢተር (ንብበሊታ) የተሰኙ ወፎችን ከሙሩሌ በኪዞ ቱርሚ የሚሄደው መንገድ ላይ እያየሁ ፣ ለየት ያለ ነገርም ሳስተውልም እየጠየቅኩኝ እና ከእለቱ የወፍ ስም አስተማሪዬ እየተረዳሁ ደስ የሚል ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ ለምሳሌ ቢኢተር የሚባሉት ወፎች፣ መኪናችንን እየተከተሉ፣ መኪናው ሲበር አካባውን ረብሾት የሚነሱትን ነፍሳቶች ሲቀልቡ ሳይ “ግርግር ለሌባ ይመች” የሚለውን የአማርኛ አባባል አስታውሰውኛል፤ ፎርክ ቴልድ ድሮንጎ የምትባለው ወፍ ስም ስሰማ ደግሞ በልጅነታችን ፣ ድሬዳዋ ጭራ ፓስታ ብለን እንጠራት የነበረችውን ወፍ አስታውሶኛል፡፡ ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የሚገርመው ግን የነዚህ የወፍ ስሞች ጥራዝ ነጠቅነት ነው፡፡ ገንፎና ጎመን እየቦጨቀ አጣብቆ በሚኖረው የኦም ነዋሪ መሃል ያለችን ወፍ፣ “ባለ ሹካ ጭራዋ” ብሎ መጥራት ምን ማለት ነው፣ እኛ ሰፈር ውስጥ ጫኩሊስና ጭራ ፓስታ እያልን የሰጠናቸው ስሞች፣ እነ “ግንደ ቆርቁር”፣ “ሰጎንና” “ጥንብአንሳ” ን የመሳሰሉ እጅግ ገላጭ ስሞች ከፈረንጆቹ ስሞች ግጥም አድርገው ይሻላሉ ባይ ነኝ፡፡

በተለይ አንዳንዶቹ ወፎችማ እዚሁ ኦሞ እየኖሩ፣ አግኝቷቸው ከሞተ ሃምሳ አመት በሞላው ፈረንጅ ስም “ቮንደር ዲከንስ ሆርንቢል” ወይም “ብሩስስ ግሪን ፒጅን” ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነ “እርኩምና ጭልፊት”፣ እነ “የጎልያድ ሳቢሳና ጅግራን” የመሳሰሉ ስሞች ለሁሉም የሚያወጣላቸው ጠፍቶ ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በኦሞ ያሉትን ወፎች አሰያየም፣ ከአዲስ አበባው የቦሌ ሰፈር ወላጆች የስም ምርጫ ለይቼ ላየው ይከብደኛል፡፡

በቱሪዝም ኢንስቲቱዩት ውስጥ ተማሪ ሆኜ የሰማሁትና፣ “የአስጎብኚነትን ሞያ ትችት ውስጥ ጥሏል!” ተብሎ የሚታወቅ አንድ የድሮ “ውሸታም” ጋይድ የተመለከተ ወሬ ነበር፤ ከአመታት ቀደም ብሎ የወፍ አስጎብኚ ተብሎ ከወፍ ጎብኚዎች ጋር ወጥቶ በስም የማያውቃቸውንና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ወፎችን በጉብኝታቸው ወቅት ሲያጋጥማቸው እና ሲጠይቁት ይህ የድሮ ጋይድ እንደመጣለት የአገራችንን የሴት ስሞች “አበበች”፣ “ፈለቀች”፣ “ፀሐዬ” ፣ ወርቄ እና “ብርያለች” እያለ ፣ የወፎቹ መጠሪያ ነው ብሎ እንግዶቹን ሲያሳስት ከርሞ ሲመለስ፣ በሃላፊዎቹ “የሞያው አሰዳቢ” ተብሎ ከስራ መባረሩን እንደሰማሁ አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ የነኚህን ወፎች ስያሜ ሳስብ ያ የጥንቱ የወፍ ጋይድ፣ ለኢትዮጵያ ወፎች በጠቅላላ ስም ቢያወጣ እንዲህ ጥራዝ ነጠቅ ስያሜ ወፎቹ ሁሉ ባልያዙ ነበር እንድል አስብሎኛል፡፡

Secretary Bird at Omo Valley

የመንገዱን ፈታኝነት ፣ በአዲሱ የወፍ ትምህርት ሃሳብ ተጠምጄ ሳይታወቀኝ የመጀመሪያው የሃመሮች መንደር ጋር ደረስን፡፡ ሳሚ በአፈታሪኩ ከነገረን “የባኦባብ” ዛፍ ጋር አንድ አይነት ዝርያ ያለው፣ የበረሃ ፅጌረዳ ዛፍን እዚህም እዚያም እያየን ቱርሚ ደረስን፡፡ ቱርሚ ልክ እንደ ሃመሮች ባህሪ አንዳች ረጋ ያለና ረጋ የሚያደርግ ልዩ ድባብን የተላበሰች አነስተኛ መንደር ናት፡፡ በዚህ እለት ታዲያ ሁሉ ነገር በእቅዳችን መሰረት ሄዶ በግዜ ፣ የመጣንበት ድርጅት በባለቤትነት ባጠረው ካምፕሳይት ሁሉ ነገራችንን ከትመን ለሶስት ቀን ቆይታ ተዘጋጅተን ነበር፣ ሳሚ አጠር ላለ ቆይታ ባረፍንበት ካምፕ አካባ ያለን መንደር እንጎብኝ ብሎ ይዞን የሄደው፡፡

ሃመሮችን ከሙርሲዎች ጋር አንድ ላይ በእንቁዋ የኦሞ ሸለቆ ያኖራቸው ፈጣሪ ምንም እንኳን በባህሪና በሁለንተነቸው እጅግ የተለያዩ ቢሆኑም ፈፅሞ አልተሳሳተም፡፡ እንደውም የታላቁን የኦሞ ሸለቆ ጉብኝት መልክ የሚሰጠው የሁለቱ ብሔሮች ልዩነት ይመስለኛል፡፡ አንድ ሙርሲንና ሐመርን በአንድ ጉዞ ሄዶ የሚያይ ጎብኚ የሚሰማው ስሜት አንዱን እንዲወድ ሌላኛውን እንዲጠላ በሚያደርግ የልዩነት ስሜት ውስጥ ሳይሆን የሚገባው ሁለቱንም ለየግል ውበት እና ባህላቸው እጁን ከፍ አድርጎ አፉ ላይ እንዲጭንና እንዲገረም ነው የሚያደርጉት፡፡ እንዴት ለሚል እስቲ በዚህ ለእኔም ለእንግዶቼም የመጀመሪያ በነበረው ጉዞዋችን ሰባተኛ ቀን የሐመሮች መንደር በሆነችው ቱርሚ ደርሰን ፣ የሐመሮች መንደር ድረስ ሄደን ሾፎሮ የሚባለውን ቡናቸውን ጋብዘውን፣ መሸት ሲል ደግሞ ውቦቹ የሐመር ልጃገረዶችና ጎረምሶች ባንድ ላይ ሆነው የምሽት ጭፈራቸውን ኢባንጋዲ እያሳዩን የተሰማኝን ስሜት በማስረዳት ላረጋግጥ፡፡

ድብን ብለው የጠቆሩት ሙርሲዎች እጅግ ሞቃት በሆነውና በፀፀ ዝንብ ንክሻ በታጀበው መኖሪያቸው ተቀበሉን፤ ጠያይሞቹ ሐመሮች ደግሞ በተቃራኒው በነፋሻው ቱርሚ ልብ በሚሰልብ ፈገግታ አጫወቱን፤ ሙርሲዎች ጋር የነበረን የሃምሳ ደቂቃ ቆይታ የብዙ ቀን ያክል ሲረዝምብን፣ በሐመሮች መንደር ከሁለት ሰአት በላይ ጭፈራ እያየንና ከቡና ገለባ የሚሰራውን ሾፎሮን እየጠጣን ስንቆይ ግማሽ ሰአት ያክል እንኳን የቆየን ሳይመስለን ተቀመጥን፡፡

Eban Gaddi at Hammer

ግን ግን፣ የማይረሳው የሙርሲዎች ባህላዊ ሁናቴ (ሴቶቹ ከንፈራቸውን ለውበት መበሳታቸው፣ እንዲሁም ወንዶቹ ከመሃንነት ጋር በሚያያዘው እምነታቸው ምክንያ እርቃን ) እና አጠቃላይ ሁኔታ ሐመሮችን እንደ ፍፁማዊ ውቦች እንዳየን እንድንቀበላቸው አድርጎናል፤ በኢባጋዲ የምሽት ጭፈራ ወቅት ወንዶቹ እየዘለሉ የሚሽኮረመሙ የሚመስሉትን ሴቶች በሁለት እግሮቻቸው መሃል እግራቸውን እያስገቡ፣ ወሲባዊ ግንኙነት በማስመሰል የሚደረግን የተራክቦ አይነት አቀጣጣይ እንቅስቃሴ፣ መለመላቸውን ከሚታዩት የሙርሲ ወንዶች እርቃን አንፃር የጨዋ አተያይ በልባችን አይተን ውድድ እንድናደርጋቸው ሆኗል፡፡ ለእኔ ግን ሁለቱም ተመጋጋቢ ናቸው፡፡ እንደውም ከእንግዶቹ እንደተረዳሁት፣ የሙርሲዎችን አይነት ገሃድ የወጣ ባህል በቃ ከዚህ በኋላ አናይም ማለት ነው ሲሉ ስለነበር ድንገት በሐመሮች መንደር ያየነው ትእይንት በሙሉ በእራሱ እንደ ክብሪት ሆኖ እሳት አቀጣጥሎ ይኸው እስከዛሬ ልረሳው የማልችለውን አስገራሚ ክስተት በአንድ የሐመር ጎረምሳ እና በእንግዳችን መካከል እንዳይ የራሱን አስተዋፅኦ ተጫውቷል፡፡

በዚህ የአጭር ጊዜ ቆይታ ምክንያት ታዲያ የጎብኚዎቻችን አጠቃላይ ስሜት እስከ መጨረሻው ድብልቅልቅ ያለ እንዲሆን የሚያደርግ ያልተጠበቀ ክስተት ይፈጠራል፡፡ ከስፔን ከመጡት ባልና ሚስቶች ጋር የነበረችው ስፔናዊት ቀበጥ፣ ፈቅዳና ወዳ በራሷ ላይ ዱብዳ ጋብዛ፣ የጉብኝታችንን ቅርፅ ታምታታብናለች፡፡ ነገሩ እንዲ ነው፣ የሐመር መንደር ሄደን ጭፈራ በምናይበት ወቅት ሲጨፍሩ ከነበሩት የሐመር ጎረምሶች መሃል “ሙጋ” የተባለውን (ኋላ ከእኔ ጋር እንዲሁ ለአመታት ወዳጅ ሆነን ልንዘልቅ) የሐመር ጎረምሳ ወድጄዋለሁና ከርሱ ጋር ነው የማድረው ብላ አገር ይያዝልኝ ትላለች፣ ይህቺው የስፓኒሽ ጎብኚ፡፡ አይሆንም ተብላ ብትለመን ብትሰራ ሞቼ እገኛለሁ፣ የማድረውም እዚሁ በመንደራቸው ነው ብላ ገግማ አደረች፡፡ ካደረች በኋላ የሆነውን “ዝገርም” በቀጣይ ክፍል እቀጥላለሁ!!!

ይቀጥላል!

በያሬድ ይልማ

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!

Leave a Comment