ጉዞዬ ክፍል አስራ አራት | በያሬድ ይልማ

ማንም ቢሆን እግዚያብሔር ሲፈጥረው ስሜትና ፍላጎት አለው፡፡ ሃይማኖት፣ የግብረገብ ትምህርቶች፣ ስልጣኔ፣ ማህበረሰባዊና ቤተሰባዊ አስተምህሮቶች እንዲሁም ባህል፣ ሁሉም ዬራሳቸውን አሻራ ያሳርፉብንና በተፅእኖዎቹ ልክ እኛም በሰው ፊት የምናንፀባርቀው ፆታዊ ማንነት አሊያም ስሜት ይኖረናል ማለት ነው፡፡ ሙርሲዎች እርቃናቸውን የሚሄዱባቸው ፣ ሐመሮች ኢባንጋዲ ላይ በምሽት የሚደንሱበት መንገድ የራሳቸው ባህላዊ ምክንያት አላቸው፣ የግድ ከፆታዊ ግንኑነት ጋር መገናኘት የለበትም፡፡ ከአውሮፓ በተለይ በተመጣጣኝ ሞቃታማ ከሆነው ክፍለ አህጉር የሚመጡት እንደ እስፓኒሽና ጣሊያን አይነት ጎብኚዎች ግን ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ፆታዊ ዝንባሌያቸውን በግልፅ ማንፀባረቅ የሚወዱ እንደሆኑ በአመታት የቱሪዝም ቆይታዬ የማረጋግጥ ቢሆንም ይህ የመጀመሪያዬ ጉዞም ግልፅ መነፅር ሰጥቶኝ አልፏል፡፡

ከካሮዎች ምድር ቆይታችን ወደ ሃመሮች እምብርት ቱርሚ የመጣነው በእለተ ሰንበት በመሆኑ ፣ በነጋታው ሰኞ ከእኩለ ቀን አካባቢ ጀምሮ በዚያው በቱርሚ በሚኖረው የሃመሮች ገበያ ለመታደም እና እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ሃመሮችን ለማየት እንግዶቻችን በጉጉት እያሰቡ፤ ነበር የእለተ እሁዱ የቱርሚው ቆይታ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት ባለው የጉዞ ተረክ እንደተናገርኩት፣ በተፈጠረው ያልተጠበቀ የወደድኩት ጥያቄ ምክንያት የእንግዶቻን ቁጥር በአንድ ቀንሶ ፣ አራ ሴት ይዘን ወደ ሃመር መንደር ጭፈራ ልናይ የሄድን ሰዎች ሶስት ሴት ይዘን የተመለስነው፡፡

በምሽት ዳንሱ ወቅት ከሃመር ልጃገረዶች ጋር ሲደንስ የነበረውን “ሙጊቲን” የእኛው ከስፔን የመጣች እንግዳ ደጋግማ እየተጠጋች አብራው ልክ ከሃመር ሴቶቹ ጋር ወንዶቹ ሲደንሱ እንዳየችው ለማድረግ ስትሞክር ቆይታ በስተመጨረሻ በምን ትግባባው በምን በማናውቀው መንገድ፣ አብራው ከርሱ ጋር ማምሸትና ማደር እንደምትፈልግ ነግራው እሱም ተስማምቶ ፣ ይቺ ቀበጥ የስፓኒሽ ሴት ይሄንን ጉድ (በድንገት ከሙጊቲ ጋር ለማደር መወሰኗን) ከጭፈራው መሃከል ተቀምጠን የሚያምረውን የሃመሮች ዳንስ እንታደም ከነበርንበት፣ መጥታ ለሳሚ በአንድ ቃል ነገረችው፡፡

በስፓኒሽ “አፍቅሬያለሁ!” አለችው ለሳሚ፡፡ ካጠገባችን አለፍ ብሎ ከተለኮሰው እሳት ፈንጠር ብለን ተቀምጠን ከነበረበት ሳሚ ለሁለት ተዘርፍጠን ቁጭ ካንበት መሬት ላይ እሾክ እንደወጋው ሰው ተስፈንጥሮ አይኑን እንዳፈጠጠ ተነሳ፡፡ የእሱን አነሳስ አይቼ እኔም የመጣውን እንግዳ ነገር ለማወቅ ቸኩዬ ተነሳሁ፡፡ ሳሚ ባማርኛ፣ “አፍቅሬያለሁ ትለኛለች እንዴ በአንድ ሰአት ውስጥ” ብሎ በስፓኒሽ ቋንቋ ለደቂቃዎች ነተረካት፡፡ ሴትየዋ ልጄ ከሙጊቲ ጋር የማደሯ ውሳኔ ላይ ሙጭጭ አለች፡፡

መቼም የተሰማኝን የተደባለቀ ስሜት መግለፅ ይከብደኛል፡፡ የመጀመሪያው የገረመኝ ነገር የእሷ ድፍረት ነው፡፡ እኔ ለራሴ ገና ካየኋቸው የመጀመሪያ ቀኔ በመሆኑ በዚህ በቱርሚ መንደር የማየው ነገር ደስ ቢለኝም ቅሉ፣ እነኚህን ሰዎች ለመልመድ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ነው የሚገባኝ፣ ሁለተኛው ደግሞ በዚህ ፍጥነት ከኋላው በሳሚና በሴቷ እንግዳችን መሃል የሚደረገውን ምልልስ አንገቱን መሬት ላይ አቀርቅሮ ፣ በተነጋገሩ ቁጥር ወደሱ እየተጠቋቆሙበት ሲነጋገሩ ላለማየት ተደፍቶ ሲሳቀቅ ሳየው፣ ምን እያሰበ እንዳለ ለመረዳት እየሞከርኩ፣ በቃ ሳሚ ምን ይገግምበታል፣ አለሙን ይቅጭ በቃ እሷ ፈልጋ ነው እያልኩ ደግሞ በሌላ በኩል አስባለሁ፡፡

ለማንኛውም እኔም ባስብ ሳሚም አይቻልም ሊል ቢሞክር የዚያችን ሌሊት ክስተት ማንም ሊያቆመው ስላልቻለ ይሄዋ ዛሬ ካስራአራት አመታት በኋላ እኔም እንድፅፈው፣ ብዙ ለድርሳን አይበቁም ስለዚህ ኤካተቱም ብዬ ካለፍኳቸው አልፍ አእላፍ ትዝብቶቼ ሁሉ በላይ የዚህች ስፓኒሽ ምርጫ በዚህም ምክንያት የሚከተለን ነገር ፈፅሞ የማልረሳው የጉዞዬ ታላቅ ማስታወሻ ሊሆን ችሏል፡፡

የስፓኒሽ እንግዳችንን ማደሪያ ቢያንስ እንይ ብለን ሄደን ቤቱን እና ልታድር የምትችልበትን ብቸኛውን የቆዳ ምንጣፍ፣ ከመንደሩ ጎጆዎች አንዱን፣ የሙጊቲ ማደሪያ የሆነውን አይተን፣ እንግዲህ ለወገቧ ብርታቱን እየተመኘንላት ወደ ካምፕ ሳይታችን ተመልሰን አደርን፡፡ በነጋታው ጠዋት ይህቺው የስፓኒሽ እንግዳችን፣ ጨው መስላ፣ የካምፕሳይታችን ስትደርስ ግን የደነገጥኩት አደነጋገጥ ሌላ ነበር፡፡ እንደዛ በደስታ ስትዘል፣ ይሄንን ሲጋራ በደስታ ብዛት በላይ በላይ እየለኮሰች አፍቅሬያለሁ ብላ እንደዛ እንዳልሆነች  በአዳሯ በደረሰባት ነገር፣ ምስኪኑ ሙጊቲ፣ በድንጋጤ ጨው መስሎ፣ በጠዋት በምርኩዝ ካምፕሳይታችን ጋር አድርሷት እንዳያሳስሩህ ሲባል ፈርቶ እስከመሰውር በሚያደርስ መልኩ ያልተጠበቀ ትእይንት ምስክሮች ሆንን፡፡ አይ ከዛ በኋላ ያቺን ስፔን ያየ በሙጋ አይጫወትም ብሎ መዝጋ ይሻላል እንጂ፣ ጎብኚ ሳይሆን ታማሚ ነው ይዞን የቀረውን ስራ የጨረስነው፡፡

ማንም ሰው ምን ሆና ነው ብሎ ቢጠይቀኝ መልስ የለኝም፡፡ ግን አንድ ነገር ብቻ ልናገር እችላለሁ፡፡ ከሙጋ ጋር አድራ ከመጣች በኋላ ባሉት ቀናቶች ማየት ከነበረባት ቦታዎች ግማሹን አላየችም፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፣ በተለይ ረጅም ርቀት በመኪና ስትሄድ በየተወሰነ ኪሎሜትር መኪና እየቆመላት ወደ ጫካ ውስጥ ገብታ ትፀዳዳ ነበር፡፡ ሳሚ ተንኮለኛው የዛኑ ቀን፣ ማለትም ሰኞ ቀን ማታ አካባቢ ላይ፣ ልጁን፣ “ሙጊቲን” ማየት ተፈልግ እንደሆነ ሲጠይቃት፣ በምን አይነት ፍጥነት፣ “ኖ ኖ ኖ ኖ!” እንዳለች አልረሳውም፡፡

ከዚህ ስራ በኋላ ምርጥ ወዳጄ የሆነው ሙጋ ይሄንን አስቂም አሳቃቂም ገጠመኝ ከኔ ጋር በተገናኘን ቁጥር ስለማነሳበት ብዙ እንነጋገር ነበር፡፡ ታዲያ የእውነት ያፍር ይናደድ ነበር በተከሰተው ነገር፡፡ እነም አንድ ጊዜ እያሳቀኝ እንዲሁ፣ በመሃል “ሙጊቲ ግን ምን አድርገሃት ነው እንደዛ የሆነችው” ብዬ ስጠይቀው የመለሰልኝ መልሰ ትንሽ ግልፅ ምስል ሰጥቶኛል፡፡ እንዲህ ነበር ያለው፤ “ኢኔኮ ሴቲዮ ካንቴ ጋር ባቃ ታኛሎ ሲትል፣ ኢሺ ብዬ፣ ከሰፈር ሊጆች ጋር ሲናገር ጊዜ፣ የሴፈር ልጆች ዳግሞ፣ በዳንብ አስደስታት፣ ፈረንጅ ስለሆነች ትረዳሃለች ላንቴ ሲላሉኝ፣ በቃ በዳንብ ተኛሁ ኬሷ ጋር፤ ሴትዮ ግን ባሽተኛ ሆነ፣ ምን እንደሆነ ኢንጃ” ብሎ ነበር ክስተቱ ለሱም ቢሆን ምሽቷን ደስ የሚል አደርግላታለሁ ብሎ ከልክ በላይ ሄዶ ኖሮ ያልጠበቀው ድንጋጤ እንደፈጠረበት ያካፈለኝ፡፡

ታዲያ ይህ ጉደኛ ቀን (ሰኞ-የሐመር ገበያ ቀን) በዚህ የእንግዳችን ክፉኛ መጎዳት ይጀመር እንጂ ሌላ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን የታዘብንበት ነበርና፡፡

ይቀጥላል!

በያሬድ ይልማ

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!

Leave a Comment