ጉዞዬ ክፍል አስራ አንድ | በያሬድ ይልማ

ማስታወሻ ፡ “በዚህ የ1994 ዓ. ም. የጉዞዬ ክፍል ላይ የሚጠቀሰው የሙርሲዎች መንደር መጠሪያ ስያሜው ኮምባን “ቆምባ” ብዬ በታይፒንግ ስህተት የፃፍኩት፤ ስሙን ማረም ቢኖርብኝም፣ ኋላ ላይ “ቆምባ” የሚለው ቃል በጉራጌኛ ቋንቋ ያለው ፍቺ ለዚህ የጉዞ ማስታወሻ ገላጭነቱ የጎላ በመሆኑ እንዲሁ ትቼዋለሁና ይቅርታ!!”

                                                          —-..—-

በአማርኛ ቋንቋ ለሴትም ሆነ ለወንድ ሃፍረተ-ስጋ ለሚለው ስያሜ በባለቤትነት ለሚታወቁት የሰውነታችን ክፍሎች ለምን “በቀ እና በጠ” ቃላት እንደሚጀምሩ ምክንያቱን በውል ባላውቀውም፣ በምድረ ሙርሲ እዛም እዚም ተንዘራፍፎ እና ቀጥ ብሎ የሚገኘው እሱ ብቻ ነው፡፡ የሙርሲ መንደር ከሆነው፣ “ቆምባ” ሰፈር ከማጎ በጠዋት ተነስተን ከደረስን በኋላ እግዜር በፈጠራቸው “በቁ” እና “በጡ” ዙሪያችን ተከበበ፡፡ አደራ ቁጣ እና ጡጫ አድርጋችሁ አሳስታችሁ እንዳታነቡብኝ፡፡ ባህል ይዞኝ ነው ምን ላርግ፡፡ እግዚዮ እርቃን እግዝዮ የቁ አበዛዝ፣ እግዝዮ የሚያስገራርም የጡ አበዛዝ፡፡

ሾፌራችን ገብሬ ብዙ “ቁ” እና “ጡ” ከማየት ብዛት ሁለቱ ቃላት ሳይኖሩበት የሚታይ ስፍራ አጥቶ፣ ወደ እኔ ጠጋ ብሎ፣ ልክ የቆምባ ሰው ሁሉ እኔ፣ ገብሬ ከመድረሱ በፊት የሙርሲን ህዝብ በሞላው፣ “እናንተ ጃላዎች (ጓደኞች) ፣ ሁላችሁም ቶሎ ቶሎ ብላችሁ ልብሳችሁን አውልቃችሁ ፣ የቆምባን መንደር በ”ቁ እና በ “ጡ” ሞልታችሁ ለገብሬ አሳዩት!” ያልኳቸው ይመስል፤ – “ስማ እስኪ ያሪድ! እነዚህ በእንግሊዝ ለምታናግራቸው እንግዶች፣ ይሄ ኢጦዮጵያ ነው ብለህ ነው ምትነግራቸው ዋይስ ጋምቤላ ብለህ! ፣ “እንዴት” ስል፣ “በማርያም ብዬኃሎ፣ ከፈለክ ዋላ ሶዳን ኖው ቤላቸው ዋላ ኢንጂ፣ ኢጦዮጵያ ኖው አይትበል፤ ዋኣይ ዋኣይ! ማነው ይሄ ሁሉ ሰው ማይዳ ላይ ኢንዲህ! ፣ ከብቲ እንኳ ቂጡ ሲገለጥ ቤጭራው መልሶስ ይሸፍነዋል፤ እነዚህ ወይ ጭራ ዬላቸው ፣ ጭራችሁን መልሱና እንትኑ ሼፍኑ አንላቸው!፤ “ዋኣይ ላኣይኔ ማረፊያ እንኳ ይሄ ኢንትን ፣ ያህያ ምናምናቸው ላሌማዬት ወዴይት ሊሂድ ዛሬስ! ዋኣይ ፤ አለ ገብሬ በቆምባ መንደር የሚያየው ሁሉ ለአምስቱ የስሜት ህዋሶቹ በዝተውበት፡፡

ኢቲሞጎ የሚባል፣ የዚሁ የቆምባ መንደር መሪ ሽማግሌ ወደ እኛ ተጠግቶ፣ ለእያንዳንዱ ተሸከርካሪ ፣ የኮቴ በመኪና ሃምሳ ሃምሳ ብር መክፈል እንዳለብን ነግሮን ልንከፍል ተስማማን፤ በትከሻው ላይ ተሸክሞ የነበረውን ክላሽኒኮቭ መሳሪያ መሬት ላይ አስቀምጦ ሁለቱን መኪኖቻችን መቁጠር ጀመረ፡፡ መቼስ አሁን እኔ እምናገረውን ከቁምነገር የሚቆጥርልኝ ባይኖርም የማልረሳው ትዝብቴ ነውና እለዋለሁ፡፡ ሽማግሌው ኢቶሞጎ፣ ከገብሬ መኪና የኋላ ጎማ ጀምሮ ሁለቱን ላንድክሩዘሮቻችንን የፊትና የኋላ ጎማዎቻቸውን ቆጥሮ ሲያበቃ፣ አንዱን መኪና እንደ ሁለት ቆጥሮ ፣ ለአራት መኪና ሁለት መቶ ብር የቆምባ መንደር የኮቴ ክፈሉ አለን፡፡

ሳሚ ምንም ሳይመስለው ሁለት መቶ ብር አውጥቶ ሊከፍል ወገቡ ላይ ያሸረጠውን ቦርሳ ሲከፍት ጊዜ በሁኔታው ግራ ተጋብቼ፣ ሳሚ ሰውዬው ተሳስቷል እኮ እንዴት አንድ መኪና ሁለት አድርጎ ያስባል ስለው፣ “ ይሄ ጠፍቶት መስሎህ ነው! ከኔ በላይ ሁሉን ነገር ያውቃል፣ በገገማ ሙድ ብር እየተቀበለኝ ነው እንጂ፣ የኛን ብር እንደጦጣ ፍራንክ ስለሚቆጥሩት፣ እንደውም ቆምባን ማየት የለም ከሚለኝ፣ በዚህም ከተገላገልኩ ጥሩ ነው” ብሎኝ ለመክፈል ሲጠጋው ሽማግሌው ኢቲሞጎ እውነትም ሁሉን እንደሚያውቅ ተረዳሁ፤ ብሩን እየተቀበለ፣ “ጃላ ባቆሎ ኢኮ ካጂንካ ብዙ ብሪ ኖው!” አለ፡፡ እኔና ሳሚ እንግዶቹን ላንድ ፎቶ ሁለት ሁለት ብር እየከፈሉ እንዲያነሱ ነግረናቸው ፣ እነሱ ፎቶ ሲያነሱ እውነት የማይመስለውን ትእይንት መታደም ጀመርን፡፡

ተንኮለኛው ሳሚም በተራው ፣ ሙርሲዎቹ ላይ ሊቀልድባቸው ፈልጎ የሆነ ነገር በጆሮዬ ሹክ ብሎኝ ወደ ቱኤቿ መኪናው ሄዶ ዎኪ ቶኪ ሬድዮ መገናኛውን አውጥቶ ጋቢናው ጋር ቆሞ፣ “ዋርዴር ዋርዴር፣ ይሰማል” አለ፣ እኔም የገብሬ መኪና ውስጥ ልክ ሳሚ እንደነገረኝ፣ እንዳልታይ ሸርተት ብዬ ተቀምጬ፣ “በትክክል፣ በትክክል ዋርዴር፣ ጉጢት ነኝ በትክክል ተሰምተሃል” አልኩኝ፤ ሳሚ ቀጠለና “ጉጢት ክላሽ እና መትረየስ ይዘጋጅ ባስቸኳይ” አለ፤ ደንግጬ ሬድዮውን አጠፋሁት፡፡ ባንድ ግዜ ሳሚ ያለባትን መኪና የቆምባ መንደር ጎረምሳ በጠቅላላ ከብበው ቆመው፣ ልክ እንደ መንግስቱ ሃይለማርያም ሳሚን ለመጨበጥ ይሻሙ ጀመር፡፡ ሁሉም ሳሚን ሰላም እያሉ እየጨበጡት፣ “ጃላ፣ ጃላ” ይሉት ነበር፡፡ “ጓደኛ ነን!” እንደማለት ነው፡፡ የሙርሲን ወንዶች የማን ወታደሮች በሬድዮ ተነጋግረው በመሳሪያ ከሂሊኮፕተር ላይ እንደጨፈጨፏቸው ጭራሽ ፍንጩም ስላልነበረኝ ሁኔታቸው እያሰቀኝ ነበር፡፡ ኋላ ግን በእውነት ሳሚ ሬድዮ ከፍቶ ከወታደሮች ጋር የተነጋገረ ስለመሰላቸው ፈርተውት ነበር እንደዛ የሚለማመጡት የነበረውና በጣም አሳዘኑኝ፡፡

የቆምባ መንደር ሽማግሌው ኢቲሞጎም፣ አንዷን መኪና ሁለት አድርጎ እንዳልቆጠረ፣ እኔን ሳይቀር እየተለማመጠ ማዋራት ጀመረ፡፡ እንዲህ አለኝ ትንሽ አማርኛም ይናገር ስለነበረ፣ “ሲማ ጃላ፣ ኢኔ ጃላ ሺማግሌ ኖ! ኢዚ ቆምባ ቺጊር ዬሌም፣ አድማ የሌም!” “እሺ ጃላ” አልኩት ወዲያው ቀጥሎ እንደመለማመጥ እያደረገው፣ “ሲማ ኢኔ ኢኮ ጂንካ ያቃል!” አለኝ፡፡ ጂንካ ከተማዋን አቃታለሁ ሊለኝ ፈልጎ ነው፡፡ እሚገርመኝ መስሎት እንደሆነ ገብቶኝ ፣ አፀፋዬን ለማጋነን ፈልጌ አይኔን እያፈጠጥኩ “ኦ ጂንካ ታቃሌ” አልኩት ለኢቲሞጎ፣ ኋላ ለአመታት የምንዘልቅ እልም ያልን ወዳጆች ልንሆን፤  “ኦ ጂንካ ታቃሌ” ስለው፣ ማረጋገጫ ሳይሰጠኝ፣ ሌላ ጥያቄ ደረበ፤ “ኢንዴት ኖ፣ አዲሳባባ ቲሊቅ ኖ” አለኝ፣ አርእስት አዘላለሉ ፈጥኖብኝ ስለነበር፣ በችኮላ  “አዎ አዲሳባ ትልቅ ነው” አልኩት፣ “ኢንደጂንካ ቲሊቅ ኖ” አለኝ ፣ ከት ብዬ መሳቄን እንጂ፣ ምን እንዳልኩት አላስታውስም፡፡

በብዙ “ቁ” ታጅበን፣ ብዙ “ጡ” እንደተደቀነብን፣ ፎቶ ፎቶ በሚሉ የሙርሲ ሴቶች ንዝነዛ እና በፀፀ ዝንብ ክፉ ንክሻ ተደጋግሞ ጥቃት እየደረሰብን፣ የሃምሳ ደቂቃ ቆይታችን፣ የምእተ አመት ያክል ረዝሞብን ከቆየን በኋላ በመጨረሻ ቆምባን ለባለቤቶቹ ለሙርሲዎች ትተንላቸው መኪናችንን ይዘን ወጣን፡፡ መመለስ ጀምረን የተወሰኑ ኪሎሜትሮች እንደሄድን ሳሚ በሬድዮ ሙርሲዎች መቼና ለምን ከንፈራቸውን እንደውበት መግለጫ መተልተል እንደጀመሩ ነገረንና እኔም ገብሬም ለእንግዶቻችን ሌላ ነገር ተረጎምን፡፡ ከዚያ በፊት ግን ላጭር ጊዜም ቢሆን ፣ ገብሬ፣ “ሃይለስላሴ” ባንዳ ቢሆኑ ምን እንደሚመስሉ በጨረፍታ እኔን በሆነ መልኩ አስቃኘኝ፡፡

ያው ከዚህ በፊት እንደነገርኳችሁ፣ ገብሬ መልኩ ሲታይ ከነቁመቱ ቁርጥ ቀዳማዊ ሃይለስላሴን ነው የሚመስለው፡፡ ታዲያ በደንብ ቁልጭ ያለ ምስል ገብሬን ለመሳል እንዲያመች ግን ፣ ከጃንሆይ አንፃር ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ገፀባህሪያዊ ልዩነቶች አሉ፡፡  ገብሬን በደንብ በምናብ ለመሳል፣ በጃንሆይ መልክና ቁመት ላይ የትግርኛ አክሰንት ያለው ፣ እንደ ጃንሆይ  “እኛ” እያለ ረጋ ብሎ ከሚያወራ ሰው ይልቅ ለቁጣ የቀረበ ሁልጊዜ ንግግሩን “ኢኔ” ብሎ የሚጀምር፤ ጣሊያንኛ ሲናገር ላየው ደግሞ፤ ጃንሆይ በጅቡቲ በኩል ያደረጉት የወረራ ወቅት ሽሽት ከሽፎባቸው ደወሌ ላይ ተይዘው ከጣሊያኖች ጋር አስመራ ከርመው የጣሊያን ሹፌር ሆነው ፣ ወዳገራቸው እንደመጡ አድርጎ ማሰብ ፣ የገብሬን ቁልጭ ያለ መልክ ይከስታል፡፡ በዚ ሁኔታው ሳሚ የሙርሲ ሴቶች ከንፈርን ታሪክ በሬድዮ መተረክ ከመጀመሩ በፊት፣ ለጣሊያነኛ ተናጋሪዋ እንግዳችን፣ ጃንሆይ በጣሊያንኛ አክሰንት፣ አገራቸው ውስጥ ቆምባ የሚባል መንደር፣ በዚያም ቁ እና ጡ አቸውን በየሜዳው አድርገው በሚኖሩ ዜጎቻቸው ተናድደው እያወሩ እስኪመስል ድረስ ማንጃሬ ማንጃሬ እያለ “ለሴቷ ዞላ” የቆምባን ሰዎች ገብሬ በሃሜት ከተከታቸው፡፡

እድሜ ለሳሚ ተረት፤ የሳሚ ተረክ ድምፅ በሬድዮ መሰማት ሲጀምር፣ ገብሬ ሳይወድ በግዱ ከብስጩ የጃንሆይ የገፀባህሪ ሁኔታው ተገታ፡፡ ታዲያ ሳሚ ስለ ሙርሲ ሴቶች የከንፈር አተላተል አጀማመር የነገረን አፈታሪክ እስካሁን ከሳሚ ከሰማናቸው አፈታሪኮች እጅግ በጣም ያላሳመነኝ ነበር፡፡ ታሪኩን በቀጥታ ከመናገር ይልቅ ፣ እንድተረጉም በሬድዮ ሲነገረን የተሰማኝን ስሜት በምሳሌ ቀድሜ ብገልፀው ይሻላል፡፡ ህፃን ልጅ ከጓደኞቹ እቃ ሰርቆ እጅ ከፍንጅ ይዞ የሚያውቅ ሰው፣ ይበልጥ ይረዳኛል፡፡ ህፃናት በእንዲህ አይነት ድንገተኛ ዱብዳ ውስጥ ሲገቡ እንደሚዘላብዱት ሁሉ የሳሚም ሙርሲን የተመለከተ አፈታሪክ እንደዛ መስሎ ስለተሰማኝ፣ ሳሚ አፈታሪኩን ሲናገር እየሳቀም ጭምር ስለነበረ፣ እኔም የቆምባ መንደር ሽማግሌውን የኢቲሞጎን እና የራሴን የግል ንግግር፣ “አዲሳባ ትልቁ ነው፣ ኢንደጂንካ ቱሉቅ ናው!” የሚለውን እንደ ታሪክ አርዝሜ ተናግሬ እንግዶቹን አስቄ ተገላገልኩ፡፡ ገብሬም ስላልመሰለው ለጣላኒያዊቷ አልተረጎመላትም፣ ይልቁንስ የብስጭት ንግግሩን ካቆመበት ቀጥሎ መጨረሻ ላይ ከዞላ ጋር ተሳሳቀ፡፡

የማጎ ወንዝ ላይ ለመንገድ የያዝነውን ምሳ በልተን ወደ ፓርክ ተመልሰን ጥቂት ካረፍን በኋላ፣ አውሬ ልናይ የማጎ ፓርክ ማእከላዊ ስፍራ ላይ ሄድን፤ አውሬ ለማየት የማጎ ፓርክን የክረምት ግዜ ወንዝ ሁሉ ወንዝ እየተባለ በዝርዝር የሚያሳይ ካርታ ከጀርመን ይዞ መጥቶ፣ እዚ ጋር ዝሆን ልናይ እንችላለን፣ እዚህ ጋርም ጎሽ ሊያጋጥመን ይችላል፣ እያለ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረውን የእንግዳችንን ልብ ሰብረን፣ ሶስት ቦታ የተከመረ ትኩስ ዝሆን በቅርብ የጣለው እበት እንጂ፣ የክረምት ወንዞቹንም፣ ዝሆኖቹንም ሳናይ ወደ ማረፊያችን ተቃረብን፡፡ በሁኔታው እጅግ በጣም የተበሳጨው ጆርጅ ውጪ ውጪውን እያየ፣ አለፍ አለፍ እያሉ ፓርኩን የሞሉትን የምስጥ ኩይሳዎች ከርቀት ሲታዩን ፣ በስተመጨረሻ የፓርኩን ጠባቂ ጫካ መሃል ስናይ ጆርጅ ያለወትሮው ድምፁን ከፍ አደርጎ ለእኔ ፣ “ ሉክ ኤሌፋንት” ሉክ ኤጌን አናዘር ኤሌፋንት ዜር” “ አይ ሃቭ ኔቨር ሲን ኤ ካንትሪ ላይክ ዚስ፣ ኤ ናሽናል ፓርክ ዊዛውት አኒማልስ፣ ኤ ሪቨር ዊዛውት ዋተርስ!” እያለ በሹፈት እና በምሬት ስሜቱን ገለፀ፤

ተው ቦሎው እንጂ ፣ ዋኣይ ዛሬ ጭቃ አላስቼገረን፣ ጎማ አልነፈሰብን፤ ተመስገን ቀኑ አዉነ አረጋዊ ነው እኮ፣ ተመስገን ማለት ነው እንጂ፤ “እኔ ምን ላድርግ ገብሬ እራሱ እኮ ነው የተማረረው፤ ዝሆን የሌለበት ፓርክ እያለ! ምን አድርግ ትለኛለህ” ስለው፣ “ዋኣይ አንተማ ምን አረክ!” ለጀዎርጅ ኖው እንጂ ላንተም ጡሩ አይደለም በለው ያሪድ፣ ምንም እንኳ ዝሆን ባያይም፣ ለዝሆኑ ማረጋገጫ ትኩስ እበት አይቷል! ከሁሉ ቤላይ ዳሞ፣ እራሱ ዝሆን ባይሆንም ያው የዝሆን ማለት ነውና ፣ ያንን ሁሉ የቆምባ መንደር ብልት፣ ዋላ ልዩ ጥውትም አይቷዋል፡፡ አለ ገብሬ ፈረንጁን ለማጽናናት!

ይቀጥላል!

በያሬድ ይልማ

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!

Leave a Comment