ጉዞዬ ክፍል አስር | በያሬድ ይልማ

በድካምና በፍርሃት መካከል ያለው ግንኙነት ምን እንደሆነ ጠልቆ ባይገባኝም፣ አንዳንዴ ፍርሃት ድካምን ያጠፋል ፣ አንዳንዴ ግን ድካም ይረታና ፍርሃት ሰሚ ያጣል፡፡ ለእኔም በዚህ የፓርክ መሃል አዳር ከነበረብኝ የአውሬ ፍራቻ ይልቅ ሰውነቴን ያናወዘው ድካም በልጦብኝ፣ በማጎ ፓርክ የእንግዳ ማረፊያችን ጧ ብዬ ሳንኮራፋ ነጋልኝ፡፡ ማንኮራፋትህን እንዴት ሰማኸው እንዳትሉኝ፣ የማንንም ስላልሰማሁ፣ ያው የኔ አይሎ መሆን አለበት በሚለው የማጣፋት ህግ ነው፡ለማንኛውም ፣ ከአዲስ አበባ ከወጣሁ አራት ቀን በኋላ ፣ ሁለቱን ባርባምንጭ አንዱን በኮንሶ ካሳለፍኳቸው ቀኖች የአራተኛ ቀን አዳሬ ጥሩ እንቅልፍ የተኛሁበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የዚህ ቀን የጉብኝት ትኩረት ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የቱሪስቶቹ ኢትዮጵያ መምጣትን ያጫሩትን የሙርሲ ብሔር መንደር ድረስ ሄዶ እነዚህን ኢትዮጵያዊያ ማየት ሲሆን ሁለተኛው ከዛ ስንመለስ ልናደርግ የወጠንነው፣ በዚሁ በማጎ ፓርክ የሚደረግ የእንስሳት ጉብኝት ነው፡፡

ከነበርንበት የማጎ ብሔራዎ ፓርክ ማረፊያ እስከ ኮምባ የሙርሲዎች መንደር ድረስ ያለው ርቀት ሃምሳ ኪሎ ሜትርችን አይበልጥም፤ ግን እንደዛሬ የተጠረገ መንገድ ከመሆኑ በፊት በዚህ በኔ የመጀመሪያ ወቅት፣ በ1994 ዓ. ም. ማንም በኪሎሜትር ርቀት ሳይሆን በመንገዱ ፈታኝነት ስለሚያስብ ቀድመን በጠዋት ከካምፓችን ወጣን፡፡ መረሬ የነበረው የማጎ ፓርክ መግቢያ ድረስ የነበረው ስምንት ያክል ኪሎሜትር ጭቃ፣ ለሊቱን ጠፈፍ ብሎ አድሮ ስለነበረ፣ አንድ ግዜም በጭቃ ሳንያዝ ወደ ሙርሲ በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ወጣን፡፡ በዚህ የፓርኩ የውስጥ መንገድ የማልረሳው ሳሚ ሶስት ያክል ጊዜ እያስቆመ ያሳየን ተከምሮ የደረቀ የዝሆን እበት ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ እበቱን እንዳየሁ፣ ልክ ዝሆኑን ያየሁ ይመስል እራሴም ተደንቄ እንግዶቼንም ላስደንቅ ብሞክርም፤ ኋላ ላይ ከጀርመን ድረስ እንስሳ ለማየት ጓጉቶ በመጣው ጀርመናዊ ቱሪስት፣ በዚህ እበት ምክንያት ሁላችንም መሳቂያ  እንሆናለን፡፡

አሁን አሁን ሳስበው በተለይ የሚገባኝ ነገር፣ ማጎ ብሔራዊ ፓርክ ሌላ ሳይሆን የ”ዲክ ዲክ” ወይም በአማርኛ የኢንሹ ብሔራዊ ፓርክ ቢባል ጥሩ ነበር እላለሁ፡፡ ማጎን እያቆራረጠ በሚሄደው እጅግ ፈታኝ የሙርሲ መንገድ ስንሄድ እዚም እዚያም ጥንድ ጥንድ ሆነው ውር ውር ሲሉ እያየን ነበር የማጎ ውስጥ መንገዳችን፡፡ አንድ እንገዳ ነገር ሲያይ ለዚያ እንግዳ ነገር ማብራሪያ ተረት በተጠንቀቅ አዘጋጅቶ የሚጠብቀው ሳሚ ስለ ኢንሹዎች ጥንድነት የነገረን፣ የፍቅርና የእርግማን ታሪክ ብዙ እንባ ሊራጭ ስለሚችል፣ ይህ ደግሞ በዚህ ቀን ጉዞ ያጋጠሙኝን ገጠመኞች ለዛ በሃዘን ድባብ ስለሚለውስብኝ፣ ለዛሬ በይደር ይቆይ፤ እንዲያው በደፈናው ግን ወንዱ ኢንሹ ሴቷን እንዴት እንደሚወዳት ለመግለፅ ያክል፣ ሴቷ በታመመች፣ በደቂቃዎች ውስጥ እሱም ይታመማል፣ የጠና ህመም ከሆነ እና ከተሰቃየች፣ ቀድሟት ሊሞት ሁሉ ይችላል፡፡

ጥቂት በሙርሲ መንገድ እየሄድን ታዲያ የነሳሚ መኪና ቆመና ሁሉም ሰው ድንገት ከመኪና ወረደ፣ ምን ሆነው ነው ብዬ ከነበርኩበት የገብሬ መኪና ጋቢና ግራ በመጋባት እየቀረብነው ከነበረው መሪ መኪናችን ውስጥ ያሉትን ሰዎች ለማየት እየሞከርኩኝ፣ ገብሬም ድንገት ሲጢጢጢ… አድርጎ ኮብራውን አቆመው፡፡ ገብሬ ምን ሆኖ ነው ብዬ ዞር ብዬ ደንግጬ ሳይ የሆነ ነገር ማጅራቴ ላይ ተሰካብኝ፡፡ ቀጥሎ እግሬ ላይ ሌላ ነገር እንደገና ተሰካብኝ፡፡ እንግዶቻችንም እኛም ድንገተኛ ዱብዳ ገጥሞን ከቆመችው የገብሬ መኪና እየዘለልን ወረድን፡፡

በእንግሊዘኛ መጠሪያው፣ “ፀፀ ፍላይ” ትባላለች፣ ትባላለች የሚባል እንኳ አይደለም፤ ይባላል እንበለው! የፀፀ ዝንብ ፣ አንዳንዶች እንደሚሉት የጎሽ ዝንብ ነበር የለበስኩትን ጂንስ ሳይቀር በስቶ ልክ የሚለበልብ ጫፍ ባለው ረጅም መርፌ እንደተወጋ ሰው ሁላችንንም የጠቀጠቀን፡፡ ሁላችንም እየዘለልን ይሄንን እንኳን ስሱን የእኛን ቆዳ፣ ስለት የማይበሳውን ከዱር አውሬዎች ሁሉ እጅግ ወፍራም ቆዳ ባለቤት የሆነውን ጎሽ የሚያዘልል ብስ መብሳት በሚችል ገራሚ ዝንብ ሁላችንም ደንግጠን መኪናችን ጋር እየተፈራገጥን ሳለን፣ ጥቂት ራቅ ብሎ ከሚታየኝ የፊተኛ መኪና ወርዶ ቆሞ የነበረው ሳሚ በሬድዮ ለመጀመሪያ ጊዜ እንግሊዘኛ ተናገረ፡፡ “ዌልካም ቱ ሙርሲ” አለ፡፡ ሙርሲ ሰው ሲደርስ መጀመሪያ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚሉት ፣ ያለማጋነን ያካባቢውን ሁለንተና በሚሰቀጥጠው አፋቸው አበሳስ ባንዴ የሚያቀምሱት እነኚህ ዝንቦች መሆናቸውን ለአመታት በሚቀጥለው የቱሪዝም ጉዞዬ እኔው እራሴ የማረጋግጥ ቢሆንም የሳሚ ንግግር ሹፈት መስሎኝ ነበር፡፡

ነገሩ ሁሉ ገብቶን መንገድ መልሰን ከመጀመራችን በፊት፣ ፈረንጅ የሆነ ነገር አያጣም አይደለ፣ የግመል ሽንት ፣  የግመል ሽንት የሚሸት ፣ የሆነ የቢንቢ ምስል ያለበት ፊሊት እንግዶቻችን አውጥተው ሰውነታቸው ላይ ከነፉ በኋላ ለእኔና ለገብሬም አንድ ለሁለት ሰጡን፡፡ ይሄንን የመአተኛ ዝንብ ንክሻ ሽታው ስለሚያርቀው ነበር፤ ስለዚህ ሰውነቴን በዚህ የፈረንጅ ፊሊት አለበስኩት እና ለገብሬ ሰጠሁት፡፡ ገብሬ ሽቶ የሰጡት ይመስል አንገቱ እና ጆሮው ስር ደጋግሞ ነፍቶ ፣ የመኪናው ኪስ ውስጥ አስቀመጠው፡፡ መኪናው እየበረረ ሲሄድ ልክ እንዳውሮፕላን እየበረሩ የሚከተሉንን ዝንቦች ላለማስገባት በዛ ሙቀት የመኪናችንን መስኮት ግጥም አደርገን ዘግተን እንደ ህፃን ዝንብ እንደፈራን የሙርሲዎች መንደር ኮምባ መታጠፊያ ላይ ደርስን እንደገና ሌላ እንግዳ ነገር አይተን ቆምን፡፡

እድሜያቸው ከሃያ የማይበልጡ፣ ሁለት የሙርሲ ጎረምሶች ሙሉ መለመላቸውን ኖራ ተቀብተው፣ አምላ እንደፈጠራቸው እየተንገጫገጩ መንገዱ መሃል ስለነበር ልክ ከሰማይ የወረደ መልአክ እንዳየ አማኝ ፈረንጆቹ፣ በሙርሲ ጎረምሶቹ ሁለንተና አቅላቸውን ስተው ጎረምሶቹን ከነምናምናቸው ፎቶ ለማንሳት ተግተልትለው ከሁለቱም መኪኖች ላይ ወረዱ፡፡ ሙርሲን በነፃ ፎቶ ማንሳት ስለማይቻል፣ እያዳንዳቸው ሁለት ሁለት ብር ላንድ ፎቶ ስፓኒሶቹ ሊከፍሏቸው ሳሚ ተነጋግሮላቸው ስለነበር እነሱ እያነሱ እኛ የራቁት ትእይንቱ ላይ ደረስን፡፡ እኔ በተለይ ከእንግዶቼ ቀድሜ ነው ጎረምሶቹ ጋር የደረስኩት፡፡ ሳሚ ፎቶ እየተነሱ ያሉትንና እያንዳንዷን የስፓኒሾቹን ፍላሽ እና የካሜራ ቅጭታ የሚቆጥሩ ጎረምሶች ፣ ሳሚ ዘና ሊያደርግ ፈልጎ በምልክትና ጥቂት አማርኛ ያወራቸው ጀመር፡፡ “ጃላ” አለ ሳሚ፣ “ጃላ አንቴ ሲም ማኖ” ሙርሲው በሚችለው አንድ ቃል ለሳሚ መልሶ፣ “ጎርሞሳ” አለ፤ ወዲያው ታዲያ ሳሚ እያዋራው በጎረምሶቹ መለመላ አቅላቸውን የሳቱት የስፓኒሸ ሴቶች የካሜራቸውን ፎከስ ከፊት ወደ ብልት ዝቅ እንዳደረጉት የተረዱት ጎረምሶች ተቆጥተው እጃቸውን አይሆንም አይሆንም በሚል እያወዛወዙ፣ እንግዶቹ ፎቶ ማንሳት እንዲያቆሙ እየጮኹ ተናግረው እንግዶቹንም እኛንም አስደነገጡን፡፡

እንግዶቹ በጎረምሶቹ ሁኔታ ተደናግጠው ፎቶ ማንሳት ሲያቆሙ፣ ሳሚ እየተቆጡ ወደ ነበሩት ራቁታቸውን ወዳሉት ጎረምሶች ተጠግቶ፣ “ጃላ ምንድነው ጃላ” ሲል ጊዜ ከሁለቱ ጎረምሶች አንዱ በቀኝ እጁ ወደ ብልቱ እየጠቆመና እንግዶቹ፣ ብልታቸውን ፎቶ እያነሱ እንደሆነ በምልክትና በራሱ ቋንቋ እየገለፀ አንድ ነገር ተናገረ፡፡ “ሲማ ኩላ፣ አምስ አምስ” “ኩላ አምስ አምስ” አለ፡፡ በሁለት ብር ፎቶ ለማንሳት የተነጋገረው ሳሚ ይሄንን ክርክር ቀድሞም ስለሚያውቀው ወደ ስፓኒሽ እንግዶቹ ዞሮ የሆነ ነገር ተናገራቸው፡፡ እንግዶቹ ሳሚ የነገራቸውን ነገር ሰምተው በሳቅ ፈረሱ፡፡ እንደገባኝ ከሆነ ሳሚ የነገራቸው፣ አንድ ፎቶ በሁለት ብር እንድታነሱ የተስማማሁት፣ ከወገብ በላይ ነው እንጂ ከወገብ በታች አልነበረም፣ እና ፋውል ሰርታችኋል ያላቸው ነው የሚመስለኝ፡፡ ከስፔን ተነስተው ሙርሲ ሲመጡ፣ የቦክስን ፣ ከወገብ በታች ፋውል የሚለውን ህግ እዚ እንሰማዋለን ብለው ስላልጠበቁ በሳቅ ሞቱ፡፡ ታዲያ ጎረምሶቹ እንዳሉት፣ ብልትን ፎቶ ማንሳት ይቻላል ፣ ግን ላንድ ፎቶ አምስት ብር ያስከፍላል እንጂ፡፡

ይህንን የብልት ትእይንት፣ እንግዶቹ ከፍለው እያነሱ፣ እኔና ገብሬ ደግሞ በነፃ ቆመን እያየን፣ ገብሬ አጠገቤ መጥቶ እንዲህ አለኝ፡፡ “ዋኣይ ምሽቶቻችን እዚህ አገር ካመጣናቸው፣ በዴቂቃ ይፈቱናል!” አለ፡፡ የገባው ካለ ወይ አሜን ይበል ወይ ይሳቅ፤ እኔ ግን በወቅቱ ምንም ስላልገባኝ ጆሮም አልሰጠሁት ነበር፡፡ መንገድ ላይ የሙርሲን ሰዎች ሁለመና እፍታውን ቀምሰን ፣ መንገደኞቹን ጎረምሶች ፣ ለፊትና እነሱ እንዳሉት “ለኩላ፣ አምስ አምስ” ከፍለን ሁሉም የብሄሩ አባላት፣ በተለይ ከንፈራቸውን ለውበት ሲባል የሚተለተሉትን ልናይ ወደ መንደራቸው፣ ኮምባ መንገዳችንን ቀጠልን፡፡

ከጥቂት ኪሎሜትሮች የገጭ ገጭ ጉዞ በኋላ ዝነኛው የሙርሲ መንደር ኮምባ ደረስን፡፡ በዚህ እንኳን ለፈረንጅ ለእኛም ቢሆን ከሌላ አለም ለሚመስል የባህል ትእይንት ባለበት የሙርሲ መንደር እንደደረስን መኪኖቻችን የወረሩን በብዛት፣ ከንፈሮቻችውን ተተልትለው፣ ተተልትለው፣ አንዳንዶቹ ሸክላ ጨምረው፣ ሌሎቹ እንዲሁ ትተዉት በአይናችን በብሌኑ አፍጥጠን እያየን ከመኪናችን ወረድን፣ ታዲያ ይሄንን ለስሜት ህዋሶቻችን ትንሽ ከበድ የሚል እንግዳ ትእይንት ከልክ በላይ የወሰደው ገብሬ ነበር፡፡ ያንን ሁሉ የተተለተለ ከንፈር ያላቸው የሙርሲ ሴቶች ሲያይ ገብሬ ያለው ንግግር ይሄው እስከዛሬ ከጆሮዬ እንዳቃጨለ አለ፤ ገብሬ ሴቶቹን እንዳየ የመኪናውን ሞተር አጥፍቶ እየወረደ፣ “የቅዱስ ምቻኤል ያሌ፣ ዋኣይ፣ ዋኣይ! እዚህ አገር ህጊ የለም እንዴ! እንዴዚ ሶውነታቸው ላይ ሲጫወቱ የሚናገር አንድ ሶው የሌም! ዋኣይ ፣ ዋኣይ! ትግራይ ቢሆኑ ነሮ እነዚ ሁሉ ባንድ ላይ እስር ቤት ነበር የሚገቡ!” አለ፡፡

ይቀጥላል!

 

በያሬድ ይልማ

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!

Leave a Comment