ጉዞዬ ክፍል ዘጠኝ | በያሬድ ይልማ

Mago Park road

ጉዞዬ ክፍል ዘጠኝ

እንኳን ስምንት ሰአት ላይ ከጂንካ ተነስቶ ለሚሄድ ይቅርና ቀደም ብሎ ለሚነሳም፣ ከጂንካ ተነስቶ ማጎ ብሄራዊ ፓርክ ሄድኳርተር ያለው ካምፕሳይት ማደር ቀላል የሚባል ጉዞ አይደለም፡፡ ይህ የሆነው በርቀቱ ምክንያት ሳይሆን በመንገዱ እጅግ ፈታኝነት ምክንያት ነው፡፡ እኛ በእርግጥ እዚህ የነበርነው በነሀሴ ወር ስለነበር ዋነኛ የሚባለው የዝናብ ወቅት በወራቶች ቀድሞ አልፏል ለዚህ አካባ፣ ነገር ግን ጂንካ በደጋው የአየር ንብረት ክልል ውስጥ ያለች በመሆኗ በተለይ የመጀመሪያው የጉዟችን ክፍል በመኪና ሳይሆን በኩሽኔት ላይ የምንሄድ መስሎ ነበር የተሰማኝ፡፡ ባጠቃላይ ከሃምሳ ኪሎሜት የማይበልጠውን ይህንን ከጂንካ እስከ ማጎ የሚያደርስ መንገድ ስናቋርጥ ኔሪ የሚባል ትልቅ ወንዝንና ሌላ ጥልቅ ኩሬ አቋርጠናል፡፡ በተለይ ኋላ ደግመን በማጎ ማደሪያችን ያገኘነውን የኔሪን ወንዝ ልክ ከጂንካ መውጫ ላይ ስናቋርጠው መኪናችን እስከ የሞተሩ ኮፈን ድረስ ውሃ ውስጥ ጠልቆ ለጥቂት ሰኮንዶች እንዲጓዝ ጭምር ያደረገ አስፈሪ ጉዞ ነበር፡፡

የቱኤች ሾፌሩ ፣ የገብሬን አነዳድ አይቶ ተበረታትቶ ልክ ወንዙን እንደተሻገረ በሁኔታው በመበሳጨቱ፣ “እንዴ እኔ ይሄን ሁሉ ወንዝ እንደምንቀዝፍ መች ተነገረኝ፣ መኪና እንጂ ጀልባ ነው እንዴ ይሄ ቱኤች!” ብሎ ምርር ብሎ ሲናገር ነበር፡፡ ይህንን ካለፍን በኋላ ደግሞ ትቅጥቅ ባለውና በሚያስፈራው ከኔሪ ወዲያ ማዶ ያለ የአሪ ብሄረሰብ መኖሪያዎች እዚም እዚያም ተበታትነው የሚገኙበትን እጅግ አረንጓዴ ስፍራ ስናልፍ ትንሽ መንገዱ ለጥ ያለ ዙሪያ ገባውም ደስ የሚል ነበር፡፡ ጥቂት እንደሄድን ታዲያ እነዛ በየመንገዱ የፈረንጅ መኪና ሲያዩ እንደእበድ እያደረጋቸው እንደያካባቢያቸው የተለያዩ ትርኢቶችን የሚያሳዩ ብዙ ህፃናት፣ እንዲሁም ብዙ ውሾች በየቋንቋቸው እየጮኹ መኪናችንን ይከተሉን ነበር፡፡ የውሾቹስ ይሁን ግን እንዲህ እንደ አትሌት በሚገርም ፍጥነት መኪኖቹን ተከትለው “ፓዘር፣ ፓዘር፣ ፓዘር” እያሉ እየተጣሩ የሚሮጡት ህፃናቶች ሁኔታ ገርሞኝ እየዞርኩ አያቸው ነበር፡፡ ወዲው ግን ገብሬ ፍጥነቱን ሳይወድ ተገዶ ቀንሶ አቆማት፡፡ ከፊታችን ያለው ቱኤች መንገዱ ላይ አስፈሪ የውሃ ኩሬ ሲያይ አቁሞ እየጠበቀነ ስለነበር፣ ያው እንደፈረደበት ዊሃ የማይፈራው ገብሬ ቀድሞ እንዲያቋርጥ ነበር፡፡

እነዛ የሚከተሉን ህፃናቶች፣ ይህንን ስለሚያውቁ ነበር እንደዛ የሚሮጡት! ታዲያ ልክ ኩሬው ጋር መኪኖቻችን ሲቆሙ ወዲያው እንደበነኑ እኛ ጋር እያለከለኩ ደረሱ፤ ፈፅሞ የማይረሳኝ መልክና ድምፃቸው ነበር፡፡ በሩጫው ምክንያት እንደዛ እያለከለኩ መኪናችን ጋር ሲደርሱ ሁሉም ወደ መስኮቶቻችን ላብ በላብ ሆነው እጃቸውን ስጡኝ በሚል አኳኀን ዘርግተው እየተጠጉ፣ “ፓዘር፣ ፓዘር፣ ፓዘር” የልጆቹ ሁለነገራቸው አንጀቴን ስለበላኝ፣ አነደኛውን ህፃን መስኮቴን ዝቅ አድርጌ፣ “ፓዘር ምን፣ ምን እንስጥህ፣ ፓዘር ምን” ስለው ልጁ ማለክለኩንም ድምፁን ዝቅ አድርጎ መልሶ እንደዛው እጁን የሆነነ ነገር ስጠኝ በሚል ወደእኔ ዘርግቶ፣ “ኢ፣ ፓዘር፣ ኢ ፓዘር ፣ ፓዘር” አለኝ፡፡ ባዶ ሃይላንድ አውጥቼ ሰጠሁት፡፡ ሃይላንዷን ይዞ መልሶ ወደሰፈሩ የሮጠው ሩጫ በፍፁም ካይኔ አይጠፋም፣ አንድ ሁለቴ ወደኋላ እየሮጠ መልሶ ገላጦኝ ፍጥነቱን ሲጨምር፣ ድንገት ከመኪናው ወርጄ ሃይላንዱን በቃ አምጣ ብዬ ተከትዬው ሁሉ የምቀማው እንደመሰለው ነው የገባኝ፡፡

Deeper than expected

ኩሬው ውስጥ መኪናችን ሰምጦ እየቀዘፈ ወጥቶ ቱኤቹ ሲሻገር ከመኪናችን ወጥተን ቆመን እያበረታታን አገዝነው፡፡ ከዚህ ኩሬ በኋላ የነበረው መንገድ የማጎ ብሄራዊ ፓርክ ክልል መሆኑን ለማወቅ ሳሚን መጠየቅ አስፈላጊ አልነበረም፣ ምክንያቱም የጫካውን መጠቅጠቅና የምናቋርጠውን አሰገራሚ የዛፎች ሽፋን የያዘ ዙሪያገባ በማየት በቀላሉ ገምቶ ማወቅ ይቻላል፡፡ የተሰማኝ ስሜት ሁለት አይነት ነበር፡፡ አንደኛው አዲስ ነገር ለማወቅ ላለው ውስጣዊ ጉጉቴ እንሰሳ አያለሁ የሚል ቀና የሆነ ስሜት ሲሆን ሁለተኛው ግን ንፁህ ፍራቻ ነው! ምክንያቱም አካባቢው ሁሉ ፀጥ ያለ ጥቅጥቅ ደን ነበርና፡፡ ትንሽ ከተጓዝን በኋላ ደግሞ መንገዱ እራሱ እጅግ የሚያስፈራ ሆኖ አገኘነው፡፡ ዳገት እና ቁልቁለት የሚበዛበት የማጎ ፓርክ ጥርጊያ መንገድ ባብዛኛው የመንገዱ ርዝማኔ ግማሹ በጎርፍ ተሸርሽሮ ገደል ሆኖ ስለነበር መኪናችን በተወሰነ ዲግሪ ተንጋልሎ ነበር በመንገዱ ላይ ይሄድ የነበረው፣ በተለይ አንዳንድ ቦታዎች ላይ መኪናው እጅግ ከመንጋለሉ የተነሳ የምንገለበጥ ይመስል ነበር፡፡ ለቶዮታ ስሪት መኪኖች ከፍተኛ አድናቆት እንድሰጥ የተገደድኩበት ይህ የመጀመሪያ አጋጣሚዬም ነበር፡፡

በተለይ ወደ ሙርሲ ሃና የሚወስደውን መንገድ በስተቀኝ ትተን ወደ ግራ ለስምንት ያክል ኪሎሜትሮች በሚረዝመው መንገድ ያደረግነው ጉዞ የመጀመሪያው ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ይህ እስከ ፓርኩ ማረፊያ የሚያደርስ ለስምንት ያክል ኪሎሜትሮች ብቻ የሚረዝም የጥቁር አፈር መንገድ ላይ ሁለቱ መኪኖቻችን በድምሩ ስድስት ጊዜ በጭቃ ማጥ ይያዛሉ ሁለት ጊዜም ጎማ ተንፍሶ ይቀይራሉ፡፡ ሁለቱንም ጊዜ የተነፈሰው ጎማ የእኛ መኪና ነበር፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የኋላ ጎማችን ሲተነፍስ ወደ መከናችን መጥቶ፣ “እዚ መኪና ውስጥ ከነጀናባው የመጣ ሰው አለ” ብሎ አሾፈ፡፡ ትንስ በቱሪዝም ስቆይ ይህ የእውነትም እንደእምነት ተከትሎኝ እኔም ጎማ በተነፈሰና አንድ ከባድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር መልሼ እኔም፣ “ዛሬ ማነው ከነጀናባው የመጣው” እንደምል አላውቅም ነበር የሳሚን ንግግር እንደሰማሁ፡፡

ይሄን የከሰአት በኋላ መከራ የሆነ መንገድ ጨርሰን አመሻሽ ላይ ማጎ ፓርክ ማረፊያ ስንደርስ ገብሬ ፣ በጭቃ ሲያዝና ጎማ ሲተነፍስበት ሁለንተናው ተጎሳቁሎ፣ መልኩ ከጃንሆይ ይልቅ መንግስቱ ሃይለማርያምን መስሎ ነበር የደረስነው፡፡ የፓርኩ ሬንጀር ጠባቂዎች ምግብ ስንሰራ የሚያግዘን አንድ ታዳጊ የአሪ ልጅ እና ለድንኳን መጣያነት የተሰራውን ማደሪያችንና እኛንም ጭምር እንዲጠብቀን የተቀጠረልንን ባለ ጠመንጃ ጠባቂ ይዘን ቁጥር አምስት የሚባል ካምፕሳይት ጋር አመራን፡፡ ካምፕሳይቱን ደርሰን ስናየው ደስ የሚልም፣ የሚያስፈራም ገነት ነው የሚመስለው፡፡ ረዛዝመው እና እርስበርስ ተጋጥመው ጥላ የሰሩት በድንኳን መጣያ ካምፕሳይቱ ያሉት ዛፎች፣ ቅጠሎች፣ ሃረጎች እና የአእዋፍ ዝማሬ አቅል የሚያስት ውበት አለው፣ በተለይ እዛው ካምፕሳይታችንን አቋርጦ ሷሷሷ.. እያለ የሚፈሰውና፣ ጂንካን እንደወጣን ተሻግረነው የመጣነው “የኔሪ” ወንዝን ላየ እውነትም ገነት መሃል ልናድር ነው ያስብላል፡፡ ግን ደግሞ ይሄ ሁሉ ውበት መልሶ በፀጥታውና ከሁሉ በላይ አንበሳና ዝሆን የሚተራመስበት የማጎ ፓርክ መሃል ላይ ድንኳን ውስጥ ልናድር መሆኑን ሲያስቡት የአእዋፍ ድምፆቹም ሆነ የነብሳት ስርስርታው፣ ፍርሃትን በላይ በላይ ሹክ የሚል ነገር አለው፡፡

እድሜ ለተማርኩበት የቱሪዝም ኢንስትቲዩት ስልጠና ከሳሚ ጋር እና ከተመደበልን ረዳት ጋር እየተጋገዝኩ ለእንግዶቻችን እራት ሾርባ እና ፓስታ ለመስራት እኔ ተፍ ተፍ ማለት ጀመርኩ፡፡ እቃ ሊያጥብ የመጣውም ልጅ ቀላል የሚባል እርዳታ አይደለም የረዳኝ፡፡ እንደምንም፣ በወረቀት የታሸገውን ብትን ሾርባ (ኢንስታንት ሱፕ) በደቂቃዎች ውስጥ ወደ ሾርባ ቀይረን ፓስታ ጣድን ከዚያ በኋላ ስጎ መስራት እና ካርባምንጭ መውጫ ላይ የገዛነውን አሎሎ የሚያካክል ማንጎ አጥቦ ማዘጋጀት ብቻ ስለነበር፣ ያንን ብርቱና ታዛዥ ረዳት፣ እዛው ከቅርባችን ለእንግዶች ተብሎ ከተዘጋጀው ፓምፕ እየተደረገ የሚቀዳ የጉድጓድ ውሃ በጀሪካን እንዲያመጣልኝ እየነገርኩ ሁሉንም ችክን አድርጌ አዘጋጀሁ፡፡

ሳሚ ጠረቤዛ ዘርግቶ ማቀራረቡን ለልጁ ሃላፊነቱን ሰጠልኝና፣ ላብና ጥቀርሻ የወረሰውን ገላችንን ኑ እናፅዳ ብሎ ሁለቱ ሾፌሮቹንና እኔን እየመራን ወደ ኔሪ ወንዝ ሳሙና ይዘን ሄድን፡፡ የፈረንጅ ነገር ውሃው ውስጥ ሲነከሩ ቆይተው፣ እነርሱ ከነበሩበት ከወንዙ ክፍል ጥቂት ወረድ ብለው የነበሩ ድፋርሳ ወይም ባማርኛ ውድምቢ የሚባሉ የሜዳ ፍየል አይነት ዝርያ እየተንሾካሸኩ ፎቶ እያነሱ ነበር፡፡ ምንም እንኳን እኛም አይተን የማናውቃቸው የእንሰሳ አይነቶች ቢሆኑም ቅሉ ሳንጓጓ ልብሳችንን አወላልቀን ጥልቀቱ ወገብ ድረስ የሚሆነው የኔሪ ወንዝ ውስጥ እኔና ሳሚ ቀድመን ተነከርን፡፡ የወራጁ ወንዝ ውሃ ሲነካኝ እዝጊዮ የተሰማኝ ስሜት ደስ ሲል፡፡ ታዲያ ወዲያው ከኛ ቀጥለው ተከታትለው ገብተው የነበሩት ሾፌሮቻችን የቱኤቹ ሾፌር ልክ ወንዝ ውስጥ ገብቶ በገባ በሰኮንዶች ውስጥ፣ ኡ፣ ኡ፣ ኡ፣ እያለ እዘለለ ወደ ዳር ሮጦ ወጣ፡፡ በሱ ጩኸት ፈረንጆቹ ፎቶ እያነሷቸው የነበሩት ውድንቢዎች በርግገው ሲሄዱ ፈረንጆቹ እየሳቁ ያዩን ነበር፡፡ ተደናግጠው ኔሪ ዳር ቆሙትን ሾፌር ሳሚ ፈገግ ብሎ፣ “ምን ገጠሞት አባት” ሲል እንደዛው ሳይረጋጉ “እንዴ እኔንጃ እባብ መሰለኝ እግሬን ሲነክሰኝ እኮ ነው ዘልዬ ያመለጥኩት” አሉ ቁና ቁና እየተነፈሱ፡፡ ሳሚ “እረ አያስቁኝ እባክዎትን፣ እርስዎን ሊነድፍ ሲጠብቅ የነበረ እባብ ነው! እዚ እባብ የለም፣ ትንንሽ አሶች ናቸው! ዝም ብለው ነው የሚቆነጥጡት አይፍሩ ይግቡና ይታጠቡ ይልቅስ” ሲላቸው ሳያምኑት ፣ መታጠቡን ትተው በህብረት ወደተጣሉት ድንኳኖች ተመልሰው ሄዱ፡፡

ታጥበን ጨርሰን እኔና ሳሚ ሆነን እራት እንግዶቻችን ልናበላ የተሰራውን ስጎ ከነጩ ፓስታው ጋር ለማቀላቀል ፣ ፓስታ የቀቀልንበትን ድስት ሳጣው ግዜ ረዳቴን ጠርቼ፣ ፓስታውን የቱ ጋር እንዳደረገው ጠየቅኩት፡፡ የመለሰልኝን መልስ እንኳን በውኔ በህልሜም አልጠበቅኩ፡፡ “የተቀቀለው ፓስታ የታለ?”  ብዬ ፓስታ የቀቀልንበትን ድስት የሚመስል ድስት ንፅት አድርጎ አፉ ውዝት ብሎ የቆመውን ረዳቴን ጠየቅኩት፣ አይኖቹን በተማፅኖ አስተያይ አይን አይናችንን እያየ “ ኢ ፓስታ ኖ፣ ቤላሁት!?” አለኝ፡፡ እኔ በድንጋጤ ደረቅኩኝ ሳሚ ደግሞ በሳቅ ፈነዳ! ሁለት ሙሉ ፓስታ ለዚያውም ነጩን ያለስጎ፡፡ ምን ይደረግ እንግዶች ሾርባ እስኪጠቱ ድረስ እየተጣደፍን መልሰን ሌላ ሁለት ፓስታ ለማመን አቅቶን ቀቀልንና እንግዶችን አበላን፡፡ ሁሉ አልቆ ሁለተ ሁለት ሆነን የምናድርበት ድንኳን ውስጥ ፣ ከገብሬ ጋር ላድር ስገባ በባትሪ ብርሃን እየታገዘ ገብሬ ልክ እንደ ሮሃ ባንድ ጊታሪስት ገላውን ይፎክታል፡፡ የወንዙ ውሃ ይሁን አላውቅም የእኔም ሰውነት ማባበጥ ጀምሮ ነበር፡፡ ታዲያ እንቅልፍ ሊያሸልበን ሲል፣ ሳሚ ከእንግዶች ጋር የእራት ጠረቤዛ ጋር ቁጭ ብሎ እያወራ ስለነበር ፍርሃቱን የሚካፍለው አጥቶ የነበረው የቱኤቹ ሾፌር ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ጋሽ ገብሬ?” አለ ገብሬ አሸልቦ ስለነበር ድምፄን ዝቅ አድርጌ “አቤት” አልኩ “እዚ ቦታ ብዙ አውሬ አለ አይዶል?” አለ “አዎን” አልኩኝ፤ “አያርገውና አንበሳ ሌሊት ቢመጣብን ምን እናደርጋለን” አሉ ሰውዬው ፍርሃት አላስተኛ ብሏቸው፤ ጥያቄያቸው የኔን ፍርሃት እስተወዲኛው አጥፍቶ ሳቄን አመጣብኝና እንዲህ አልኳቸው፤ “ እንበላዋለን!”

ይቀጥላል!

በያሬድ ይልማ

ኢትጵያዊነት ይለምልም

Leave a Comment