እውን ከወይንሸት የተሻለ ታጋይ አለን? (ኤርሚያስ ቶኩማ)

Ethiopia: እውን ከወይንሸት የተሻለ ታጋይ አለን? (ኤርሚያስ ቶኩማ)

እኛ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከራሳችን ጉድፍ ይልቅ የሌላው ሰው ጉድፍ ጎልቶ የሚታየን፤ የእኛ ስኬት በሌሎች ውድቀት ላይ የተመሠረተ ነው ብለን የምናስብ እየሆንን ይመስለኛል፡፡ ይህንን እንድል ያስገደደኝ ሰሞኑን በወይንሸት ላይ እየተሰነዘሩ የሚገኙትን የወረዱ ስድቦችን በመመልከቴ ነው፡፡

ወይንሸት ባለፉት ጥቂት አመታት ብቅ ካሉት የሀገራችን ጥቂት እውነተኛ ወጣት ፖለቲከኞች መካከል አንዷ ነች፤ ስንቱ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ፎርም በሞላ ማግስት ለቪዛ ጥያቄ ወደኤምባሲ በሚያመራበት በዚህ ወቅት የተሻለ ሀገር ሄዳ መኖር ስትችል ሀገሬን እንዳለች እዛው ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ እኩል እየተሰቃየች የምትገኝ ለእውነትና እና ለፍትሃዊነት ስትል የምትታገል ወጣት ፖለቲከኛ ነች፡፡

ይህችን ወጣት ከሚተቿት ግለሰቦች መካከል አንዳንዶቹ ሠላማዊ ታጋይ ነን ይሉ የነበሩና ከኢትዮጵያ ሲወጡ ሠላማዊ ትግል አያዋጣም ሲሉ የሰማናቸው የቪዛ ፖለቲከኞች ናቸው፤ በነገራችን ላይ ሠላማዊ ትግል ካላዋጣ መሄድ ያለብህ አሜሪካ ሳይሆን የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ አርበኞች የሚገኙበት ኤርትራ ሊሆን ይገባ ነበረ፡፡

ሆኖም ወትሮም ፖለቲካን ለጥቅም ብለው የገቡበት ስለነበረ ከሀገር ሲወጡ ኤርትራ በረሃ ገብተው የትጥቅ ትግሉን ከመቀላቀል ይልቅ አሜሪካና አውሮፓ ቁጭ ብለው በፌስቡክ እንደወይንሸት ያሉ ጠንካራ ፖለቲከኞችን ሲተቹ ይውላሉ። ማንም ሊክደው የማይችለው ግን በአመክንዮ ከተወያየን ከዚህ ዘመን ፖለቲከኞች አንድም ግለሰብ ወይንሸት ሞላን የመተቸት ሞራሉ ይኖረዋል ብዬ አላስብም ለነገሩ ወይንሸትን እየተቿት የሚገኙት በረሃ ወርደው እየታገሉ የሚገኙት አርበኞች ሳይሆኑ እዚሁ ፌስቡክ ላይ 24 ሰአት ተቀምጠው በግንቦት 7 ስም የጥገኝነት ወረቀት ስለወሰዱ ብቻ እራሳቸውን እንደታጋይ የሚቆጥሩ ግለሰቦች ናቸው እነዚህ ግለሰቦች ከራስ ወዳድነታቸውና ከባዶ ጩኸታቸው የተነሳ ግንቦት 7 እስካሁንም ድረስ ውጤታማ እንዳይሆን ምክንያት የሆኑ ግለሰቦች ይመስሉኛል።

እነዚህ ግለሰቦች በረሃ ወርደው ድርጅታችን የሚሉትን ቡድን ለመቀላቀል ቅንጣት ያህል ድፍረት የሌላቸው ግለሰቦች ከመሆናቸውም በላይ ምንም አይነት ጥቅም የሌላቸው ግለሰቦች ናቸው። በጣም የሚያሳዝነው እንደፕሮፌሰር ብርሃኑ ያሉ ታላላቅ ግለሰቦች ከተስተካከለ ህይወት ይልቅ የህዝቤ ነፃነት በማለት በረሃ ወርደው ነፍጥ ሲያነሱ እነዚህ የማይጠቅሙ ተራ ልወደድ ባይ ግለሰቦች በረሃ ወርደው ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ጎን እንደመቆም እንደወይንሸት ያሉ ቆራጥ ፖለቲከኞችን ሲተቹ ይውላሉ።

እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ልጆች የማክበር ልምዱ የሌለን በመሆኑ እንጂ ወይንሸት እየከፈለችው ያለችው መስዋዕትነት አውሮፓውያን ብዙ የሚያወሩላት ሮዛ ሉክሰምበርግ ከፈፀመችው ተግባር የማይተናነስ ነው። ወይንሸት በኢትዮጵያ እንዲፈጠር እየታገለችለት ያለው አጠቃላይ ማህበረሰባዊ ለውጥ ሮዛ ሉክሰምበርግ ከታገለችለት የማህበረሰብ ለውጥ ቢብስ እንጂ አያንስም።

ሰላማዊ ትግል ያዋጣል ካልክ እንደነWoyinshet Molla ሐገር ቤት ከወገንህ እኩል መከራ እየተቀበልክ መታገል ነው፤ ይህ አያዋጣም ካልክ የትጥቅ ትግል እያካሄዱ የሚገኙትን ወገኖች ገብተህ ተቀላቀል። ካልሆነ ግን አሜሪካ ሆነ አውሮፓ ተቀምጠህ ታጋይ ነኝ የምትል ከሆነ ልታፍር ይገባሃል። ኦንላይን የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ በፌስቡክ ሥልጣን የለቀቀ የ3ኛው አለም የፖለቲካ ድርጅት የለም። አሜሪካ እና አውሮፓ ተቀምጠህ ሰላማዊ ትግል አያዋጣም እያልክ ሰላማዊ ታጋዮችን እየነቀፍክ ከምትውል እንደጀግኖቹ ታጋዮች በረሃ ወርደህ የትጥቅ ትግሉን ስትቀላቀል ለወይንሸት ሞላ የተሰጠው ክብር ላንተም ይሰጥሃል።

ኤርሚያስ ቶኩማ

Leave a Comment