ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር ማጠናከር ትፈልጋለች- ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ከር ማያርዲት ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ ዘርፍ ያለውን ትብብር ከፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገለፁ፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት ሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ ዘርፎች የነበራቸው ትብብር ስኬታማ ነበር ነው ያሉት ሳልቫ ኪር፡፡

ደቡብ ሱዳን ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር የጋራ ወታደራዊ ስልጠናዎችን እና ምክክር በማድረግ ልምድ ማካበቷንም ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር ኩኦል ማንያንግ ጁክ ቀጣናዊ እና ክልላዊ ሰላምና መረጋጋትን በዘላቂነት ለማስፈን የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ግንኙነት መጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ኢታማጆር ሹም ጀኔራል ሳሞራ የኑስ የተመራውን የልዑክ ቡድን ከሸኙ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቁርጠኛ መሆኗን በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት መከላከያና ደህንነት ሃላፊዎች የሀገራቱን የጋራ ድንበር ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ላይም መወያየታቸውን ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሱዳን ትሪቡን

Ethiopia: ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር ማጠናከር ትፈልጋለች- ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር

Leave a Comment